ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ዋና ኃላፊ ቱርሃን ሳልህና ሌሎች የልማት ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ያደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ።
ዋና ኃላፊው ቱርሃን ሳልህና ምክትል ኃላፊው ክሊዎፋስ ቶሮሪን ጨምሮ በጉብኝቱ ለተሳተፉ የልማት ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴንና ሌሎች አመራሮች ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን፥ ወራሪው ቡድን እስካሁን በተደረገ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን አብራርተዋል፡፡
በርካቶች የሥነ ልቦና ጉዳትና ጫና እንዲደርስባቸው መደረጉን ጠቁመው፥ ተቋማት ለኀብረተሰቡ መስጠት በሚገባቸው አገልግሎት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም መናገራቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።