ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ጥምረት የሚመራው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ850 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ አሸንፎ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ሴክተር መሰማራቱ ይታወሳል።
በዚህም ኩባንያው በኢትዮጵያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የቴሌኮም አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችለውን የቴክኖሎጂ ማሟያ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
እስካሁን ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለቁሳቁስ ግዥ ከ300 ሚሊያን ዶላር በላይ ያወጣው ሳፋሪኮም በቀጣይ አስር ዓመታት ውሰጥ በኢትዮጵያ 8.5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መዋዕለ ነዋይ ኢንቨስት ያደርጋል ተብሏል።
የታዋቂው የቴሌኮም ኩባንያ ቮዳኮም ቤተሰብ የሆነው ሳፋሪኮም ከሚሰጠው መደበኛ የቴሌኮም አገለገሎቶች በተጨማሪ በተከታታይ በሀገሪቱ የዲጂታል ዘርፍ የጎላ ሚና ይኖራቸዋል የተባለላቸውን በፋይናንስ፣ በትምህርት፣ በጤና በግብርና፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በርካታ አገልገሎቶችን ለመስጠት ማቀዱ ተነግሯል።
ኩባንያኛው በአሁኑ ሰዓት 200 ኢትዮጵያውያንን ቀጥሮ እያሰራ የሚገኘ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ እስክ 1,000 የሚሆኑ አዳዲስ ሰራተኞች ኩባንያውን ይቀላቀላሉ ተብሏል። በተመሳሳይ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ይፈጥራቸዋል በተባሉ የተለያዩ የዘርፉ ዕድሎች በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ለ1.6 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ ያስገነባውን የመረጃ ቋት ማዕከል ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል።
የኩባንያው የውጭ ጉዳይና ቁጥጥር አፊሰር ማቴ ሃሪሰን ሃርቬይ፤ ሳፋሪኮም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን የቴሌኮም ጥራት ለማሟላት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃን የተላበሰ የአገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የሚጠበቅበትን ግዴታ ለማሟላት እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
በፈረንጆቹ 2023 ዓ.ም. 25 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ህዝብ ለማዳረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሳፋሪኮም በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በአዳማ የገነባቸው የመረጃ ቋቶች እያንዳነዳቸው እስክ 10 ሚሊየን ደንበኖችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሲሆን ኩባንያው በቀጣይ ተመሳሳይ ማዕከላትን በዘጠኝ ከተሞች እንደሚተክል ታውቋል።
ዋና መሥሪያ ቤቱ ናይሮቢ የሚገኘው ሳፋሪኮም የኬንያ የቴሌኮም ድርጅት ሲሆን ኬንያ ውስጥ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢና በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።
የኢትዮ-ቴሌኮም የመሰረተ ልማት አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለውን ውይይት እያደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰው ኩባንያው ከጥቂት ወራት በኋላ የድምጽ የጽሁፍና የኢንተርኔት አገልግሎት ይጀምራል ነው ያሉት።