ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመጀመሪያ የሃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበት ደረጃ ከ 2015ቱ የሶስትዮሽ ሥምምነት ጋር የሚፃረር አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለ፤ በቅርቡ የመጀመሪያ ዙር የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ቀድሞውኑ ግንባታው በታችኞቹ ተቀባይ አገራት ምንም አይነት ጫና እንደማያሳድር ስትገልፅ የቆየችው አቋሟን ዳግም ያፀና መሆኑን ገልፀዋል።
ግንባታውና ሀይል የማመንጨት ምዕራፉ ከ2015 የሶስቱ አገራት ሥምምነትን የሚፃረር ስለመሆኑ በግብፅና ሱዳን ባለስልጣናት እየተስተገባ ያለው ሀሳብ መሰረተ ቢስ ነውም ብለዋል አምባሳደር ዲና።
ግብጽ የሦስትዮሽ ስምምነት በሌለበት ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድቧ በተናጥል ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሯን በመቃወም ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፏን ይታውቃል ኢትዮጵያ በዚህ የተናጥል ርምጃዋ ዓለማቀፍ ግዴታዎቿን እና ሦስቱ ሀገሮች የፈረሙትን የጋራ የመርሆዎች መግለጫ ጥሳለች በማለት የከሰሰች ሲሆን፣ በዚህ ርምጃ ለሚደርስብኝ ጉዳት ኢትዮጵያን ተጠያቂ አደርጋለሁ ማለቷ የታወሳል።
የግድብ ግንባታውንም ይሁን የሀይል ማመጨት ሥራውን በሚመለከት ሥምምነቱ ምንም ያስቀመጠው ነገር እንደሌለ ያወሱት አምባሳደር ዲና፤ ግንባታው የተጀመረው ሀይል እንዲያመነጭ እንጅ ቆሞ እንድንሸማገል አይደለም ማለታቸውን ኤ ኤም ኤን ዘግቧል።
ግብፅና ሱዳን አሁንም የግድቡ ግንባታም ይሁን ሀይል የማመንጨት ሂደቱ ጉዳት እንደሌለው ጠፍቷቸው ሳይሆን ሀቁን ለመቀበል ካለመፍቀድ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ዲና፤ ኢትዮጵያ አሁንም በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል::