ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሕወሓት ዳግም በተቆጣጠራቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች ከአንድ ግለሰብ ከአምስት እስከ 10 ሺሕ ብር በማስገደድ እየሰበሰበ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት የሕወሓት ታጣቂዎች ከነዋሪዎቹ አስገድደው የሚሰበስቡት ብር ብቻ ሳይሆን አንድ ኩንታል ጤፍና ማሽላ ጭምር ነው ተብሏል፡፡
ሕወሓት ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ በአዋሳኝ አካባቢዎች ዳግም በጀመረው ጥቃት ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ለአብነትም ከራያ አላማጣ ወደ ቆቦ ከተማ 15 ሺሕ ሰዎች፣ ከዋግኽምራ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ወደ ፅፅቃ እና ሰቆጣ ከተማ ከ30 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
የሕወሓትን ጥቃት ተከትሎ የአላማጣ የተለያዩ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁን ድረስ ወደ ቆቦ ከተማ እየተፈናቀሉ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ የሕውሓት ቡድን ከየካቲት ስድስት 2014 ጀምሮ ከአንድ ሰው እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ብር እና አንድ ኩንታል እህል አስገድዶ የመሠብሰብ መመሪያ አውጥቶ ዘረፋ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡
ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉና ሰሞኑን ከአላማጣ ወደ ቆቦ ከተማ የገቡ አንድ ግለሰብ፣ ታጣቂ ቡድኑ በአላማጣ ዙሪያ በሚገኙ ቀበሌዎች በመዘዋወር ከአንድ ሠው እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ብርና መቶ ጣሳ እህል በግዴታ እየሠበሰበ ነው ብለዋል፡፡
ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው በዋጃ፣ ጥሙጋ፣ ሰሌን ውኃ፣ አቦ ኩርማ እና በሌሎችም ቦታዎች ነው ያሉት፣ እያንዳንዱ ግለሰብ “መቶ ጣሳ ማሽላ ወይም ጤፍ፣ ከአምስት ሺሕ እስከ ሰባት ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ከብቶች ጭምር በግዴታ አምጣ እየተባለ ነው” ሲሉ የተመለከቱትን ተናግረዋል።