ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት 2 ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረምን የመምራት ኃላፊነትን ከኬኒያ መረከቧ ተገለጸ፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ከኬንያ የሰራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ሚኒስትር ከሲሞን ቼሉጉዊ ጋር ገንቢ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሚኒስትሯ የሰራተኞች ፍልሰት አስተዳደርን በማሻሻል ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸው ገልፀዋል፡፡
ላለፉት ሁለት አመታት በኬንያ የተመራ የ11 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት ቀጠናዊ የሰራተኞች ፍልሰት መማክርት የሚኒስትሮች ፎረም በርካታ ተግባራትን ሲያካሄድ መቆየቱም ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም የመሪነቱን ሚና ለተጫወተው የኬንያ መንግስትና ለፎረሙ አባል ሀገራት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብለዋል ወ/ሮ ሙፈርያት፡፡በሀገራት የስራ ገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለገበያ ማቅረብ የሀገራቱን ኢኮኖሚ ከመደገፉም ባሻገር ዜጎች የሚገባቸውን ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
በቀጠናዊ የሚኒስቴሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረሙን የመምራት ሀላፊነት ኢትዮጵያ መቀበልዋ ገልፀው የአመራር ሽግግሩ በቅርቡ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በዚህ ዘርፍም የተሰጣትን የመሪነት ሚና ቀጠናዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ትሰራለች ተብለዋል።