የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መፍረሱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን መፍረሱ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሶስት ዓመታት በፊት በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን የተቋቋመበትን ዓላማ ሳያሳካ መፍረሱ ተገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠው የስልጣን ዘመን መገባደጃ ላይ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የስልጣን ጊዜ እንዲራዘምለት ጠይቆ ነበር። እስካሁን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል የኮሚሽኑን የሥራ ጊዜ ለማራዘም ዝግጁነት እንደሌለ ተነግሯል።

ይህንን ተከትሎ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ቢሮውን ከነቁሳቁሱ እንዲሁም ከዘንድሮው በጀቱ የቀረውን በሙሉ በቅርቡ ለተቋቋመው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲያስረክብ በቃል መታዘዙም ታውቋል።
ኮሚሽኑ በሥራ በቆየበት 3 ዓመት መንግስት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲመድብለት የነበረ ሲሆን፤ በሥራ ዘመኑ መጠናቀቂያ 2014 በጀት ዓመት ከ21 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ በጀት ተይዞለት ነበር።

ከሃምሌ ወር 2013 ጀምሮ የሥራ ዘመኑ እስካበቃበት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ኮሚሽኑ ከተመደበለት በጀት ከ4 ሚሊዮን ብር በላዩን የተጠቀመ ሲሆን ቀሪውን ለምክክር ኮሚሽን እንዲያስረክብ ታዟል።
የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ግጭትና ቁርሾን በአገራዊ እርቅ ደምድሞ ሰላም የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ይፈጥራል፤ ለዘመናት የዘለቁ ግጭቶችን መንስኤ ከመሰረቱ በማጥናት መፍትሄ ለማምጣት ያግዛል ተብሎ የተቋቋመ ነበር።

በተጨማሪ በዳይና ተበዳዮችን የመለየት ሥራ ሰርቶ ይቅር ያባብላል፣ ሌሎችም በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነትና ግዴታ ተወጥቶ ኢትዮጵያን ሰላም ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም ፍሬውን ሳያሳይ የሥራ ዘመኑ ማብቃቱ ተገልጿል።

LEAVE A REPLY