ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር በበኩሉ በዓሉ በሚኒልክ አደባባይ ተጀምሮ የተለመደው የእግር ጉዞ ወደ አደዋ አደባባይ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ በሕልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት አስቀድሞ የተያዘዉ መርሃ ግብርም የሚገልጸዉ በዓሉ እንደተለመደዉ በሚኒሊክ አደባባይ በማርች ባንድ እና ሰልፈኞች ባሉበት የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ተደርጎ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ እንደተለመደዉ በእግር ጉዞ ወደ ታሪካዊዉ አድዋ ድልድይ በመሄድ በቦታዉ ትርዒት እና ንግግሮች ይቀርባሉ፡፡

በትናንትናው ዕለት የወጣው ደብዳቤ ላይ የተቀመጠዉ ትርዒት የሚቀርብበት እና ንግግር የሚደረግበት ቦታ ብቻ መጠቀሱን ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል፡፡

አድዋ የሕብረት፣ የአንድነት፣ የመደማመጥ እሴት ያለዉ በመሆኑ በዓሉን ሲከበር በሕብረት በአንድነት እና በአሸናፊነት መንፈስ ማክበር እንዳለብን መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸዉ የተፈጠረዉ ክፍተት የመናበብ እና ደብዳቤዉ ሲጻፍ የበዓሉን ማጠቃለያ ቦታ ብቻ በመግለጹ የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዉ በዓሉ እንደተለመደዉ በሚኒሊክ አደባባይ እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡

በማርች ባንድ የታጀበ የአበባ ጉንጉን ከተቀመጠ በኋላ ለብዙ ዓመታት ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ወደ አድዋ ድልድይ የእግር ጉዞ በማድረግ ሲኬድ እንደነበረዉ ዘንድሮም ወደ ቦታዉ በእግር እንደሚሄድ እና በቦታዉም ትርኢት ቀርቦ እና ንግግር ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

መላዉ ኢትዮጵያዉያን ለበዓሉ እንኳን አደረሳችሁ ያሉት ልጅ ዳንኤል ወጣቶች ተተኪዎች በመሆናችሁ የአገራቸው ጋሻና ጦር በመሆን ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረዉን ማንኛዉንም መጥፎ ነገር እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

LEAVE A REPLY