ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ከተሳነው ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ፈጥሮ እንደሚታገል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣን ድረስ የሰርጎ ገብ አደረጃጀት አለው ያለው ፓርቲው፤ መንግስት የህዝብ ደህንነት እንዲያስጠብቅ እና መዋቅሩን በጥልቀትእንዲፈትሽ አሳስቧል።
ኢዜማ ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ አርብ የካቲት 25፤ 2014 በአዲስ አበባ የሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የዛሬው የኢዜማ መግለጫው ትኩረት ካደረገባቸው አምስት ነጥቦች አራቱ በጸጥታ እና ግጭት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር የዳሰሰው የኢዜማ መግለጫ አንዱ ክፍል በተደጋጋሚ ጥፋት እየፈፀመ ነው ያለው ኦነግ ሸኔ ቡድን በተመለከተ ነው አዜማ በመግለጫው የሽብር
ቡድን በሚል የተጠራው ኦነግ ሸኔ ፤ በመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ድጋፍ በማግኘት አላማውን በማስፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኦነግ ሸኔ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የኢኮኖሚ እና ቁሳቁስ ድጋፍ የሚያመቻች ምስጢራዊ ቡድን አዋቅሯል ሲል ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ገልጿል። የሽብር ቡድኑ ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ድረስ የሰርጎ ገብ አደረጃጀት አለው ሲል አስታውቋል ቡድኑ ባደራጀው ምስጢራዊ ቡድን መረጃዎችን ያገኛል ብለዋል።