የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተባለ

የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ በየእለቱ እያሻቀበ የመጣው አለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ የኢትዮጵያ የነዳጅ ግዢ ወጪ በእጥፍ በመጨመር 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ዓመታዊ የነዳጅ ወጪን ለመሸፈን በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ 4 ሚሊዮን ማትሪክ ቶን የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች ያስገባል።

ጦርነቱን ተከትሎ በአለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 140 ዶላር ደርሷል።
በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለአለም ገበያ የምታቀርበው ሩሲያ ከሳኡዲ አረቢያ ቀጥሎ ከአለም ኹለተኛዋ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች አገር እንደሆች ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ሃ/ማርያም ለኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ እንደተናገሩት፤ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 140 ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የምታስገባው የተጣራ የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ከዚህም የሚበልጥ በመሆኑ የነዳጅ ዋጋ ንረት በዚሁ ከቀጠለ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታችንን ለመሸፈን 6 ቢሊዮን ዶላር ሊያስፈልግ ይችላል ብለዋል።

ይህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊሸከመው የሚችል ባለመሆኑ ከወዲሁ ነዳጅን በቁጠባና በሀላፊነት መንፈስ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የገለፁት ታደሰ በህገወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ ክትትልና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY