ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ናዝራዊት አበራን በቻይና ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ለእስር እንድትዳረግ ምክንያት በሆነችው ጓደኛዋ ላይ የ15 ዓመት እስራትና የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተላለፈባት::
ስምረት ካህሳይ የተባለችው ተከሳሽ ልዩ ፍቃድ ሳይኖራት በህዳር ወር 2011 ወደ አገር ያስገባችውን 5 በሻምፖ እቃ የታሸገ ኮኬይን ዕፅ ተበዳይ ናዝራዊት አበራ የተባለች ጓደኛዋን ወደ ቻይና አብረን እንሂድ ብላ በማግባባት ቪዛ እና የአየር ትኬት ካስጨረሰች በኋላ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ለናዝራዊት አበራ ሰው ሰራሽ ጸጉር ማጠቢያ ነው ቻይና ውሰጅልኝ ካለቻት በኋላ እርሷ ግን የአባቷን ሞት ምክንያት በማድረግ ትቀራለች፡፡
ተበዳይ ናዝራዊት አበራም ቻይና ደርሳ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገባት ፍተሻ የያዘችው 5 ሻምፖ መሰል 5 ኪሎ ግራም የሚመዝን የኮኬይን ዕፅ መሆኑ ተደርሶበት ለእስር አንድትዳረግ ምክንያት በመሆኗ ተከሳሽ ሁኔታውን ያልተገነዘበችን ሰው በመጠቀም በፈፀመችው መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ እፆችን ወደ ውጪ አገር መላክ ወይም ማዘዋወር ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባታል፡፡
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ቀርባና ክሱ ተነቦላት “በዐቃቤ ህግ የተመሰረተብኝን ክስ ተረድቸዋለሁ ፤በተመሰረተብኝ ክስ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም፤ ምክንያቱም ለጓደኛዬ ለናዝራዊት አበራ የሰጠኋት የኮኬይን ዕፅ ሳይሆን የፀጉር መታጠቢያ ሻምፖ ነው፤ በዚህም ጥፋተኛ አይደለሁም” ስትል የእምነት ክህደት ቃሏን ሰጥታለች።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ÷ የተከሳሽን ጥፋተኝነት የሚያስረዱ 8 የሰው፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢሜግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ የተገኙ ዝርዝር የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡
ይህ ስጋት የገባት ስምረት ካህሳይም የማስረጃውን ሁኔታ ጥፋተኝነቷን በጉልህ ማሳየቱን ስትረዳ የሚቀጥለውን ቀጠሮ በመፍራት ከቅጣት እንደማታመልጥ ሲገባት ለጊዜው መሰወሯ ተመላክቷል፡፡
በከሳሽ ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ ስምረት ካህሳይ መካከል የተደረገውን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎትም ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኗ በበቂ ሁኔታ መረጋገጡን አንስቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ለመስጠት የካቲት 25 ቀን 2014 በዋለው ችሎትም ተከሳሽ በ15 ዓመት እስራትና በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንድትቀጣ ወስኗል፡፡
የኢሚግሬሽን ዜግነት የወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ ተከሳሽ ስምረት ካህሳይን ወደ ውጪ አገር ስትወጣ ወይም ወደ አገር ውስጥ ስትገባ ተከታትሎ በመድረስ ለፌደራል ፖሊስ አሳልፎ እንዲሰጥና የፌደራል ፖሊስም ተከሳሿን አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡ መዘጋቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።