በያዝነው ሳምንት 35 ሺህ የትግራይ ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ ገብተዋል 

በያዝነው ሳምንት 35 ሺህ የትግራይ ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ ገብተዋል 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ወደ ቆቦ ከተማ የሚገቡ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚገኝ የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስታወቀ። የጽ/ቤቱ ኃላፊ ዓለሙ ይመር ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በዚህ ሳምንት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ከመላው ትግራይ ወደ አማራ ክልል ቆቦ ከተማ ገብተዋል።

ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል በመግባት ላይ የሚገኙት የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው ከትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እና የጸጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉትን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ63 ሺህ 723 በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል ሥር ከሚገኙ የራያ ቆቦ 8 ቀበሌዎች፣ ከአላማጣ ከተማ እና ከአላማጣ ዙሪያ ከተሞች፣ ከባላ አካባቢ የተፈናቀሉት ሰዎች ቆቦ ከተማ በሚገኙ 4 ት/ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚኙ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም “የአካባቢው ነዋሪ ተፈናቃዮች በመቀበል እያስተናገደ ይገኛል። የፀጥታ ኃይሉም ከትግራይ ክልል የሚመጡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር በማድረግ ወደ አማራ ክልል እንዲገቡ ተደርጓልብለዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ አማራ ክልል ለመፈናቀል ያስገደዳቸውን ምክንያት ሲጠየቁ የሰላም ማጣት፣ የምርት እጥረት፣ መንግሥት አልባነት፣ ስርአተ-አልበኝነት የአደጋ ስጋትና ረሀብ በማስከተላቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ኃላፊው አንስተዋል ሲል አዲስ ዘይቤ ዘግቧል።

የዞኑ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮም ከአማራ ክልል እና ከፌደራል አደጋ መከላከልና ዝገጁነት ቢሮዎች ጋር በመነጋገር ለተፈናቃዮች የምግብና አልባሳት አቅርቦት እያደረሱ እንደሚገኙ፣ ተፈናቃዮቹ በቀጣዮቹ ሳምንታት ከቆቦ ከተማ በዞኑ ድሬ ሮቃ እና ጃራ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች እየተገነቡ ወደሚገኙ መጠለያ ካምፖች ለማዛወር ሥራዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል።

LEAVE A REPLY