ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ውስጥ ያለውን ውንብድና ለመቆጣጠር ለባንኮች አዲስ የደንበኛ ማንነት እንዲያዘጋጁ ያስቀመጠውን የግዜ ገደብ በማራዘም የኹለት ወር ጊዜ መስጠቱ ተገለፀ።
ምንጩ ያልታወቀና የህገወጥ ገንዘብ ለመከታተል ወይም በተጭበረበሩ ሰነዶች የሚገላበጠውን የገንዘብ ዝውውር ለማስቀረት ኹሉም ባንኮች ደንበኞቻቸው እነማን እንደሆኑ እንዲያጣሩ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ሁሉም የንግድ ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት እና ሙሉ መረጃ ጥንቅቅ አድርገው እንዲይዙ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ የ2 ወር ቀነ ገደብ መስጠቱን ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቧል።
ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ ሰብስበውና አጣርተው ለማጠናቀቅ ብሔራዊ ባንክ የስድስት ወር ጊዜ ሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፤ መመሪያው ደንበኞች ከሚሞሏቸው መረጃዎች ተጨማሪ ዝርዝር የደንበኛን መረጃ ጭምር እንዲጠየቁ የሚያስገድድ ነው።
በተጨማሪም ሁሉም የንግድ ባንኮች የውስጥ የደንበኛ መታወቂያ ካርድ እንዲያዘጋጁ ብሄራዊ ባንክ ማዘዙ ይታወሳል። ይህንንም ትዕዛዝ በመቀበል ሁሉም የንግድ ባንኮች ባንኮች መመሪያውን ለመተግበር ሲሞክሩ ቆይተዋል።
ሆኖም የተሰጠው ቀን ገደብ በመጠናቀቂያው ሰዓት ጥድፊያና ግርግር ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የብሔራዊ ባንክ ባንኮች የደንበኛቸውን መረጃ እንዲሰንዱ ተጨማሪ የሁለት ወር ግዜ መስጠቱ ታውቋል።