በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ውስጥ 24 የሚደርሱ የግለሠብ መኖሪያ ቤቶች በኦነግ ሸኔ የቤኒ እና ሕወሓት ታጣቂዎች መቃጠላቸውን ችግሩ የደረሠባቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
አንድ ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ በወረዳው መንደር ስድስት ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ እንደተናገሩት፣ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸውና አንድም ንብረት ማውጣት ባለመቻላቸው ከቤተሰባቸው ጋር ችግር እንደተጋረጠባቸው ጠቁመው፣ ለጊዜው አንጻራዊ ሠላም ወዳለበት ወደ አንገር ጉትን ከተማ ሒደው ከዘመድ ጋ ተጠግተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ቤቴ በታጣቂዎች ተቃጥሎብኛል የሚሉት የችግሩ ሠለባ፣ በቤታቸው የነበሩ ንብረቶች ከፊሎቹ እንደተቃጠሉ፣ ከፊሎቹ ደግሞ እንደተዘረፉ ገልጸው፣ አያይዘውም 10 ከብቶቼን ተዘርፌያለሁ ብለዋል።
ግለሰቡ አክለውም ከዚህ በፊት በመንደር አምስት ከ50 በላይ፣ በመንደር ስድስት ደግሞ ከ30 በላይ ቤቶች እንደተቃጠሉ ያስታወሱ ሲሆን፣ “እስከ አራት መቶ ኩንታል እህል በማምረት የሚታወቀው የአካባቢው አርሶ አደር ንብረቱ ተዘርፎ ችግር ላይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ሠሞኑን በወረዳው የተከሠተው የቤት ቃጠሎ ብቻ ሳይሆን፣ ቤቶቹ በሚቃጠሉበት ወቅት ንብረታቸውን ለማውጣት የሞከሩ አርሶ አደሮች መገደላቸውንና መቁሰላቸውንም ነው ማወቅ የተቻለው፡
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከዚህ በፊት ኅዳር 10/2014 የአንድ ሰው ሬሳ እንደተቃጠለባቸውና አንድ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የታገተን ሠው ለማስፈታት ሦስት መቶ ሺሕ ብር ክፈሉ ተብለው ብሩን ከከፈሉ በኋላ ሠውየው እንደተገደለ አስታውሰዋል። አያይዘውም፣ ባሳለፍነው የካቲት 29/2014 ከምሽቱ 12 ሰዓት በሊሙ ወረዳ መንደር ስድስት ንብረቱን ለማውጣት ሙከራ ያደረገ እንድሪስ አሕመድ የተባለ የ28 ዓመት ወጣት በታጣቂዎች መገደሉን ጠቁመዋል።
ከሟቹ ጋር የነበሩ ኹለት ሠዎች እንደታገቱና እስካሁን ያሉበት ኹኔታ እንደማይታወቅ ነው የጠቆሙት።
ከነዋሪዎቹ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከሊሙ ወረዳ ተፈናቅለው በአንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ 45 ሺሕ ተፈናቃዮች አካባቢያቸውን ለቀው ከወጡ ወራትን ቢያስቆጥሩም፣ እስካሁን አንድ ዙር እንኳ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ተናግሯል።