ይፈርስ የማይመስል፥ እስከ ዘላለሙ
አምና እዚህ ቦታ ላይ ፥አንድ ሱቅ ነበረ
የሱቁ ባለቤት ሚፍታህ ነበር ስሙ፤
ሙሉቀን ሲተጋ፥ በከፊል የሚታይ፥
እንደዜና አንባቢ፥ በሱቁ መስኮት ላይ
ከወገቡ በላይ፥እየተገለጠ
ለወጭ ወራጂው፥ ፈገግታ እየሰጠ
ሸቀጥ እየሸጠ
በጋዜጣ ቅዳጅ እየጠቀለለ
በልቃቂት አምሳል እየሸበለለ
“የሁለት ብር ሱካር ፥ የብር ካምሳ ዳቦ
ጢንጥየ ቅመም
ትንሽየ ለውዝ፥የሽልንግ አሻቦ፣
ከተጠቀለለው በልቃቂት አምሳል
ድሀውም ሀብታሙም ድርሻውን ያነሳል፤
“አደራው ጥብቅ ነው ፥ዱቤም አይከለክል
ባንክ አይታመንም የሚፍታህን ያክል’
“አንደበቱ ቀና፥ መዳፎቹ ትጉ
ከቶ እንደሱ የለም የትም ቢፈልጉ”
ይሉት ነበር ሴቶች ቡና ላይ ሲያወጉ
አሁን እዚህ ቦታ ፥ረጅም ፎቅ ቆሟል
ከፊት ያለው መንገድ ባዲስ ተሰይሟል
ሚፍታህ ጎዳናው ላይ ፥ዱካውን አልጣለም
የት ይሆን አድራሻው
የሚነግረኝ የለም፥
ካንደኛው ፌርማታ ወዳንዱ ስሻገር
ከሳር ከቅጠሉ የምሰማው ነገር ፥
‘የከንፈር ወዳጅህ ፥ባለፈው ተዳረች
ዘመድህ በስደት ባህር ተሻገረች
ጉልማ ታሰረ
ወንዴ ዘምቶ ቀረ
አመዴ ከሰረ
የሚል ብቻ ሆኗል
በኔ ሰውነት ውስጥ ስንት ህዋስ ከስሟል
ስንት ተስፋ ወድሟል
ስንት ስጋት ለምልሟል፥
ተጋርዶብኝ እንጂ ቀድሞ ባይታየኝ
“ደረስ ብየ ልምጣ፥ ጠብቀህ አቆየኝ”
ያልኩትን መካዱ
አደራ መብላት ነው የጊዜ ልማዱ::