ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ከተማ ለቀላል ባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ቢልቱማ ቂጣታ ገልጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት የሚፈፀመው የሥርቆት ወንጀል የአገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስተጓጎል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት ብቻ በዚሁ የቀላል ባቡር በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ከ2 ሚሊየን 197 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ርዝመቱ 1 ሺህ 363 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ሥርቆት እንደተፈፀመ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት እስካሁን ባሉት ወራት ደግሞ በገንዘብ 18 ሚሊየን 535 ሺህ 688 ብር የሚገመት ርዝመቱ 11 ሺህ 345 ሜትር ኬብል ሥርቆት መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡
በዚህም በድምሩ 12 ሺህ 708 ሜትር የሚረዝም የኬብል ሥርቆት ተፈፅሞ፤ በተቋሙ ላይ ከ20 ሚሊየን 733 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ሥርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑን የገለፁት ቢልቱማ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የራሳቸው ንብረት መሆኑን አውቀው ከመሰል እኩይ ተግባር ሊጠብቁት ይገባል ብለዋል፡፡
በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ሥርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በአገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ሥርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን፤ እንደወንጀል ድርጊቱ እየተለየ በአማራጭ በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 የወንጀል ቅጣት ድንጋጌዎቹ መሰረት በመሰል ተግባራት ላይ ሲሳተፍ የተገኘ ወይም ተባባሪ የሆነ ማንኛውም አካል በእስራትና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።