ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል እንደ ባንክ፣ ኤሌክትሪክ እና ቴሌኮምንኬሽን ያሉ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶችን ባስቸኳይ እንደገና እንዲጀምር በቃል አቀባያቸው ስቲፋኒ ዱጃሪክ በኩል ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንደሚያደንቁ ገልፀው የትግራይ ባለስልጣናትም ግጭት ለማቆም ያሳዩትን ቁርጠኝነትን አድንቀዋል።
ጉተሬዝ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ አስከፊ ስቃይ አስከትሏል ብለዋል።
አሁን የታዩት አዎንታዊ ለውጦች በፍጥነት ወደ መሬት ወርደው መተርጎም አለባቸው ሲሉም ገልፀዋል። ዋና ጸሃፊው በትግራይ ህዝባዊ አገልግሎት ማለትም የባንክ የመብራት እና የቴሌኮሚኒኬሽን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁሉም አካላት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በሙሉ ሰብአዊ እርዳታዎች ያለመስተጓጎል እንዲገባ እንዲያመቻቹ አሳስበዋል። ጉረቴዝ ሁሉም ወገኖች አሁን በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረት ግጭት የማቆም ውሳኔያቸውን ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ማሸጋገር አለባቸው ብለዋል።