ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሳዑዲ አረቢያ በእስር ቤት እና በማዕከላት ውሰጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ዜጎች ከነገ መጋቢት 21 ቀን 2014 ጀምሮ ወደ አገር ቤት መመለስ እንደሚጀምሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
እነዚህን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።
16 የመንግስት ተቋማትን በአባልነት የያዘው ኮሚቴው ዜጎችን መመለስ ለመጀመር የተደረጉ የመጨረሻ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በትላንትናው ዕለት የገመገመ ሲሆን፤ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ ዜጎችን መመለሱ እንደሚጀምር ይፋ አድርጎል።
በውይይቱ እንደተገለፀው የበረራ፣ የማቆያ ማዕከላት ዝግጅት፣ የመገልገያ ቁሳቁስ፣ የምግብ እና መጠጥ አቅርቦት፣ የአልባሳት፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የህክምና አገልግሎትን ለተመላሾች በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ በመቻል ረገድ የተደረጉ ዝግጅቶች በግብረ ሃይሉ አባላት ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት፤ የመመለሱ ተግባር ተመላሽ ዜጎችን ካሉበት አምጥቶ እስከ መኖሪያ ቀያቸው የማድረስ ሥራን የሚሸፍን ነው።
ይህንኑ ከመነሻው እስከ መድረሻው በተሳለጠ ቅብብሎሽ ለመፈፀም ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አምባሳደር ብርቱካን አሳስበዋል።
ተመላሾች አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ክልሎች ከየማዕከላቱ ቶሎ በማንሳት ወደ መኖሪያቸው መውሰድ ያለባቸው በመሆኑ ያደረጉት ዝግጅትም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ክልሎቹ ያልተጠናቀቁ የዝግጅት ሥራዎችን በቀሪ ቀናት እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።
በየጊዜው የቅበላ አቅምን በማሳደግ ዜጎችን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት፤ መንግሥት የተቻለውን ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥልም አምባሳደሯ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።