“የአህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት አመድ”
“ለአህያ ማር አይጥማትም” (በስንት ማንኪያ ማር ተሞከረች?) “የተናቀ ከተማ በአህያ ይወረራል” (በታሪክ ተዘግቦ ከሆነ ስሙ ይነገረን) …. ወዘተ በምድረ አበሻ የተነገሩ አህያን አመካኝቶ ለመዝለፍ የተፈለገን ሰውን ክብር ለመንካት ከተተረቱ በርካታ ሥነ ቃሎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ያገሬ ሰው “አህያ” ብሎ ሲሳደብ ጥቃት የማይገባው፣ ሲበደል ምላሽ የማይሰጥ፣ ክብረ በላ ደነዝ ….ለማለት ነው ፡፡
በጥንቶቹ የይሁዳ ግዛቶችም ለአህያ የነበረው አመለካከት ያው በንቀት ላይ የተመሰረተ ነበር ማለት ይቻላል። “የጽዮን ልጅ ሆይ! እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወዳንቺ ይመጣል።” እንዲል ነቢዩ ኢሳይያስ፤ ትሁት የሆነው ንጉሥ በፈረስና ፈረሰኞች ታጅቦ በሰረገላ ሳይሆን በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከደብረ ዘይት እስከ ኢየሩሳሌም በመምጣቱ ውስጥ አህያ በአካባቢው የነበራትን ሥፍራ ማየት ይቻላል።
በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም፤ አሳድዶ አይይዝም፤ እርሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝም አልታጣም ሲል እንዲሁም የነቢያቱ ትንቢት ይፈፀም ዘንድ ነው፡፡ ጌታችን የማዳን ሥራውን ወደሚፈጽምባት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ቤተ ፋጌ ሲደርስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጴጥሮስን እና ዮሐንስን ልኮ ‹‹ያስፈልጉኛልና የታሠሩትን አህያና ውርንጫዋን ይዛችሁልኝ ኑ፡፡›› ብሎ ላካቸው፡፡ እነርሱም እንደታዘዙት አመጡ፤ እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲሆን 14ቱን በእግሩ፣ 2ቱን ምዕራፍ (ከደብረ ዘይት ተራራ አካባቢ አንስቶ እስከ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ) በአህያ ሄዶ፣ ቤተ መቅደሱን 3 ጊዜ በውርንጫላዋ ከዞረ በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡
በሰውኛ ሲታሰብ ስትለፋ ውላ ምሷ ዱላና ገለባ፤ ፍዳዋን ስታይ ኖራ ስታረጅ ቀርቶ በቁሟ የአራዊት ሲሳይ የምትሆን ይህች ፍጥረት፤ በዓለም መንፈሳዊ ታሪክ ውስጥ ላንዲት አፍታ እንኳ ልታስበው ቀርቶ ከቶ ልትገምተው የማትችለው ነገር ተፈጸመባት፡፡ የደመና አክናፍ የ’ሳት ሰረገላ የሚያንስበት ፈጣሪ በእርሷ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ከበረባት፡፡ የተዋረደች እንስሳ (አህያም) በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊ ንጉሥ ክርስቶስ በትሕትናው ዙፋኑ መቀመጫ አደረጋት፤ ሸክም ያቆሰላት፥ ዱላ የሰለቻት፥ ዕረፍት የናፈቃት ‹‹ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜ ቀላል ነው›› ያለ ንጉሥ ተቀመጠባት፡፡
በኦሪት ” አብርሃምም በማለዳ ተነስቶ አህያውን ጫነ ” (ዘፍ 22÷3 ) እንደተባለ አህያ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን የይስሐቅን መሰዊያ እንጨት የተሸከመችም ናት። አህያይቱን ተሸክማ በመጣችው እንጨት በዕፀ ሳቤቅ የታሰረ ንፁህ በግ ተሰዋበት እርሱም በይስሐቅ ፋንታ የተሰዋው በግ የክርስቶስ ምሳሌ ሆነ።
ዳውላና የነጋድራሶችን ሸቀጥ ተሸክማ አገር ‘ላገር የምትኳትን ይህች እንስሳ፤ ለቅጽበት እሳተ መለኰት ዙፋኑ ያደርገኛል ብላ ልታስብ ቀርቶ ልትቃዥ አትችልም ነበር ግን ሆነ። ክብሩን በእርሷ ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፤ በብሉይ ዘመን የእግዚያብሔር ሰው በለዓም እግዚያብሔር ፈፅሞ የማይፈቅደውን ድርጊት ሊፈፅም ህዝቡን ያለጥፋቱ ሊረግም በእንስሳይቱ ጀርባ ላይ ሆኖ ጉዞ ጀመረ፡፡ ሲሔድባት ቆይቶ የእንስሳይቱ ጉዞ ድንገት ተገታ፡፡ ቆመች። በለዓም በሁኔታዋ ተበሳጭቶ ትሔድለት ዘንድ ቀጠቀጣት። ይሄኔ አህያይቱ በሰው አንደበት ተናገረችው፡፡ “ስለምን ያለጥፋቴ ትደበድበኛለህ፤ ሰይፈ ነበልባል ይዞ ከፊቴ የቆመው አይታይህም?” አለችው፤ ያ! የእግዚያብሔር መልዐክ ለእንስሳይቱ እንጂ ለበለዓም አልታየም ነበር።
ፈጣሪ በእንስሳቱ በኩል ለበለዓም ሊል የፈቀደው ነገር ነበርና እንስሳይቱን አከበራት፡፡
አህያ የእግዚአብሔርን መላዕክት ማየት ብቻ አይደለም ጌታ አምላኳን እስራኤል ከተባሉ አማኞች እንኳን ቀድማ ያወቀች ናት። ለዚህም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ደረቅ ወንጌል በተባለው ትንቢቱ ” በሬ የገዢውን አህያ የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም” ብሎ መስክሮላታል(ኢሳ 1÷3 )። ሊቀ ኃዋርያት ጴጥሮስም በመልዕክቱ
“ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብደት አገደ” እንዲል (2ኛ ጴጥ 2÷16) አህያ “ሰው ብቻ” ከተባለ ሳይሆን ነቢይ ከተባለ ሰውም በልጣና ተሽላ የተገኘችበትም እንደነበረ ነግሮናል።
ጢባርዮስ ቄሳር የሕዝብና የንብረት ቆጠራ ሊያደርግ አገሩን በሙሉ ወደ ቤተልሔም ጠራ። እንግዳ መቀበያዎች በሙሉ ከየአገሩ በተሰበሰቡ ተቆጣሪዎች በመያዛቸው፣ ማርያምና ዮሴፍ ከቤተልሔም ነዋሪዎች በአንዱ ሰው ቤት ግርግም ገለባ ጐዝጉዘው ሰውነታቸውን ማሳረፍ ነበረባቸውና ጋደም አሉ። ብርዱ ቆዳን ሰርስሮ አንጀት ውስጥ የሚገባ ዓይነት ነው፡፡ ድንገት ማርያም በምጥ ተያዘች። የበኩር ልጇንም ወለደች። እረኞች ውዳሴ አቀረቡ፣ መላዕክት ዘመሩ። ስብሃት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብ እያሉ። አህያይቱን ጨምሮ በግርግም የነበሩቱ እንስሳት ሙቅ ትንፋሻቸውን እያመነጩ ህፃኑን ሊንከባከቡት ሞከሩ። በዚህ ሰዓት የቤተልሔም በርካታ ቪላዎችና የእንግዳ ማረፊያዎች በግንዲላ ፍም ደምቀው፣ ነዋሪዎቻቸውንና እንግዶቻቸውን ለእንቅልፍ ያባብላሉ። ክርስቶስ ግን በእንስሳት ታጅቦ በእናቱ ማርያምና ዮሴፍ እቅፍ በመላዕክት መልካም ምኞት በእረኞች ዘፈን ውስጥ በግርግም ከበረ።
ክርስቶስ በተመላለሰባቸውና በኖረባቸው ጊዜያት ሁሉ ከምንም በላይ ትህትናን፣ ዝቅ በማለት ውስጥ ያለውን ክብርና በረከት ሲያስተምርና በተግባርም ሲያሳይ ኖሯል፡፡ ሆሣዕናም አንዱ ማስተማሪያው ነበር። ስመ ገናና ነው፡፡ ህዝቡም ሆነ ሮማውያኑ ቅኝ ገዢዎች ስለእርሱ ያላቸው ግንዛቤ የተምታታና ግልፅ ያለ ባይሆንም እጅግ ክብር ይሰጡት ነበር። ድውያንን ፈውሷል፤ አንካሶችን አዘልሏል፤ ከበረከቱ መና ብዙዎችን መግቧል። በድንቅ ትምህርቱ የሺዎችን አፍ አስከፍቷል። እንደሰው ቢታሰብ እንኳ ይህ ሰው በወርቅ የተንቆጠቆጡ ሰረገላዎች፣ በክብር ያጌጡ ጋሻ ጃግሬዎች ለንጉሥ የሚገባ የሠራዊት ሰልፍ ሲያንስበት ነው፤ ሊያውም የአባቱ የዳዊት ዙፋን ወደነበረበት ኢየሩሳሌም ሲገባ ግና ይህ ሁሉ ክብሩ በውርንጫ ጀርባ በህፃናት አጀብ ሆኖ እንዳይሔድ የሚከለክለው አልነበረም።
እርሱ በውርንጫዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባው የባለሰረገላዎችን ክብር ሊያዋርድ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ በምድር ላይ በቆየባቸው ሰላሳ ሦስት ዓመታት ከሶስት ወር ውስጥ ማንንም አዋርዶ አያውቅም፡፡ ብዙዎችን ከትዕቢት ባርነት ነፃ ሊያወጣ ሲል ያደረገው ነው፡፡ በክብር ደመና የሚመላለስ ንጉሥ እኛ በምንንቃት ፍጡር ላይ ተቀምጦ መሔዱ፣ ቁሳዊ የሀብት ቁልል ብቻ ኖሮን ትህትና ለጐደለን ሁሉ መልዕክቱ ግልፅ ነው፡፡
ከምንም በላይ የልብን ውስጥ ክብርና ልዕልና እንድናስቀድም እጅግ ትሁት በሆነ መንገድ ተናገረ። “ከናንተ መካከል አንድ ስንኳ ንፁህ ቢኖር እርሱ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውባት!” ብሎ ፍትህ ከመስጠት በላይ ልዕልና የታል? የሰዎችን ልጆች ኃጢያት ሊመዘግብ ከተገባ እርሱ ፈጣሪ ነውና ከፈሪሳውያኑ ይልቅ ለህጉ ቀናዒ ነው፡፡ በአደባባይ እየተመፃደቁ ድንጋይ ያነሱባት ሁሉም እንደርሷ በድንጋይ ተወግረው ሊሞቱ ይገባቸው የነበሩ ናቸው ፡፡ ‘አንቺ ሴት ሒጂ ዳግመኛም ኃጢያት አትስሪ!’ አላት፡፡ ንጽህና ድንጋይ ካስነሳ ድንጋይ ሊያነሳባት ይገባ የነበረው እርሱ ብቻ ነበር ግን አላነሳባትም “ሒጂ!” አላት። ይህች ሴት ካላበደች ዳግም ያንን ኃጥያት ታደርገዋለች? ፈጽሞ! ድንጋይ ማንሳት ሲችል ድንጋይ ያላነሳ ትሁት! እርሱ ለድንጋይ አልመጣማ።
ይህ ሰንበት በጌትንት በክብር በውዳሴና በቅዳሴ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ሽማግሌዎችና ህጻናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመስገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በክብር ሲገባ ለሰጠቸው ለተቀደስ ሰላምን ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
ከደብረዘይት ወደ ኢየሩሳሌም በውርንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ከመጀመሩ አስቀድሞ ኢያሪኮ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ኢያሪኮ ቀራጩ ዘኪዮስ ቤት። ከነ ደቀ መዛሙርቱ ሲስተናገድ ውሎ ነበር አመሻሽ ላይ ጉዞ የጀመረው፡፡ ማንም የማይጠጋው፣ ፍቅር የተነሳው፣ ሕዝብ የጠላው፣ እርሱም ሕዝቡን የጠላው ቀራጩ ዘኪዎስን “ዛሬ ካንተ ጋር ነኝ!” አለው፡፡ ሕዝቡም ‘ይሄ ከሃጢያተኛ ጋር የሚውል ሃጥያተኛ ነው!’ አለና ተግተልትሎ ሊያየው እንዳልወጣ ትቶት በቤቱ ተከተተ፡፡ ፍቅርን አይቶ የማያውቀው ዘኪዎስ ባጋጠመው ነገር ተደነቀ፡፡ ጉድጓዱን በፍቅር የሞላለት መሢህ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታና ትዕዛዝ ከቤቱ ጣሪያ ሥር አርፏል፡፡
‘ከዚህ ፍቅር በኋላ በግፍ ያከማቸሁት ወርቅና ዲናር ለምኔ?’ አለ ዘኪዎስ፡፡ የህዝቡን ወርቅ ለህዝቡ አለና ጐዳና ላይ አውጥቶ በተነው፡፡ መሢሁ በትህትናና በፍቅሩ የዘኪዎስን ደዌ ፈወሰ፡፡ ከዘኪዎስ ቤት ጣሪያ ሥር ውሎ መባውን እየቆረሰ ወይኑን አብሮት እየጠጣ ልዑሉ ከበረ፡፡ ለእርሱ ክብር ማለት የተናቁትን ማክበር ነውና!
ክርስቶስ በሁሉም ትምህርቶቹና ድርጊቶቹ ትህትናን ከፍ ከፍ ያደረገ መምህር ነበር። ይህ ትህትናው እስከ መጨረሻዋ እራት ማለትም እስከ ጸሎት ሐሙስ አልፎም እስከ ጌቴ ሰማኔ ድረስ ዘልቋል። ዝቅ ብሎ የተማሪዎቹን እግር እስከማጠብ…የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው እስከማለት።
የሆሣዕናዋ ውርንጫ ነገር ሌላም የሚያሳስበን ነገር አለ። እጅግ የተናቀ የተዋረደና ለጉልበቱ ብቻ የሚፈለግ ፍጡር እንበል ሰው አንድ ቀን በአንዳች አጋጣሚ የመለኰቱ ክብር የሚገለጥበት ሊሆን እንደሚችል ማስተማሪያም ነው አጋጣሚው። ምክንያቱም መሢሁ ከአባቱ ከዳዊት ምድራዊ ዙፋን ይልቅ የመጣበትን የትህትና መንገድ ለማሳካት ስሙር ሆነው ካገኛቸው ፍጥረታትና ሰዎች መካከል የቤተ ፋጌዋ ውርንጫ አንዷ ናትና።
መለከት ባይነፋለትም በተንቀጠቀጠ የክብር ሰረገላ ላይ ባይቀመጥም፣ ልባቸው ውስጥ የነገሠባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችና ህፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ፤ መጐናጸፊያዎቻቸውንና የአርዛሊባኖስና ጥድ ቅርንጫፍ እያነጠፉ የታላቅ ንጉሥ አቀባበል ከማድረግ ወደ ኋላ አላሉም።
ከዚህ በላይ በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው አህያ በብሉይ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ኖህ፤ ከዐበይት እስከ ደቂቀ ነቢያት ዘመን ብዙ በጎ ስራን የሰራች፣ በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ከተወለደበት እስከ ስደቱ ድረስ በብዙ ስራዎች የተሳተፈች ስለነበረች ስለአገልግሎቷ ለሆሣዕና ክብር የበቃች የተመረጠች ሆነች እንጂ ዕጣ ፈንታዋ፣ ዕድል ተርታዋ ተብሎ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ለአገልግሎቷም ዋጋዋን ለመክፈልም ጭምር መሆኑ ግልፅ ነው።
ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሴት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡
“በፋሲካ በዓል ሰሞን የእውነት አምላክ ደቀ መዛሙርት ወደ ደብረ ዘይት ቀረቡ፤ በሀገረ እግዚአብሔር (ኢየሩሳሌም) አቀበቱ ላይ ብዙ አረጋውያንና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፣ በአህያ ውርንጫ ላይ ተጭኖ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ለእነዚህ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።
(ጾመ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ)
የሰሙነ ሕማማት መግቢያ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሆሣዕና ይባላል፤ ቀጥተኛ የቃሉ ትርጉም በብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ በተፃፈው በዳዊት መዝሙር 117፤25 “ נָּא הושִׁיָעה “/አሁን አድን የሚል/ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
«ሆሣዕና» ቃሉ ከሁለት አረማይክ ቃላት የተሰራ ሲሆን ትርጉም «እባክህ እርዳ፣ አሁን አድን» ማለት ነው። እብራይስጡም ይህንኑ ቃል ወርሶ «הושענא » ሆሻአና ሲል ይገልፀዋል። አዎ «አሁን አድን፣ እባክህ እርዳን» ብሎ የአዳም ዘር ያጣውን ልጅነትና የደረሰበትን ሞት ለመላቀቅ የሚያሰማው የጩኸት ድምጽ ነው፣ «ሆሣዕና»!!!
ዳዊት ነቢይ በመንፈስ ቅዱስ ተመልክቶ ማዳኑን ሲጣራና አሁን ናልን ሲል ከዘመናት በፊት አድምጠነዋል። የውስጥ ዓይኖቹ ሩቅ አይተዋል። ማዳኑንም ሽተው እንዲህ ሲል ዘምሮለታል። «አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና» መዝ ፻፲፰፣፳፭
ሆሣዕና በአርያም ማለትም ‹በሰማይ በልዕልና ያለ፤ ከሰማይ የመጣ መድኃኒት› ማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን እና ቅጠሎችን በመንገድ ላይ እያነጠፉ ‹‹ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው›› እያሉም እንዳመሰገኑ ሁሉ ዛሬም ‹‹ቡሩክ ስሙ ለእግዚብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፡፡ ‹እግዚአብሔር ነኝ› ብሎ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ እርሱ ክርስቶስም ምስጉን ነው፤›› በማለት እናመሰግነዋለን፡፡
ሰሌን(ዘንባባ)-
እሾሓም ነው ፡-ትዕምርተ ኃይል፤ ትዕምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ዘንባባ ይዘው አመሰገኑት። እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል፡-ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ፤
ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው፡-ዋህድ ባህርይ ነህ ሲሉ፤
ከዚህም ባሻገር በዘመነ ብሉይ ኤልሳዕ ኢዩን ቀርነ ቅብዑን ይዞ ሲያነግሰው፤ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ፤ አብርሐም ይስሃቅን፤ ይስሃቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ ሰሌን(ዘንባባ) ቆርጠው ይዘው አመስግነዋልና፡፡
አህያይቱ የኦሪት ቀንበርም መሸከም የለመደች (የተለመደች ሕግ) እስራኤልም ህግን መጠበቅ የለመዱ ምሳሌ ስትሆን፤ ዕዋል(ውርንጭላ) ወንጌል ያልተለመደችም ሕግ፤ ሕግን መጠበቅ ያልለመዱ የአሕዛብ ምሳሌ ናት። ከህፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አንደበት ለክብር ንጉሥ ምስጋና የቀረበበት ዕለት ነው ሆሣዕና!
ሆሣዕና በአርያም !
“ለዚህ ታላቅ ትህትናህ ሆሣዕና በአርያም ምሥጋና በሠማይ!” ከማለት ያገዳቸው አንዳች የለም፡፡
ሆሣዕና በአርያም !!