ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሳፋሪኮም የኢትዮጵያን ግዙፍ ኔትወርክ እንዲያገኝ እና በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎቱን መስጠት እንዲያስችለው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የኔትወርክ ሽርክና ስምምነት መፈራረሙ ተገለፀ።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኔትወርክ ሳይት እና ሌሎች እንደ ኔትዎርክ ሮሚንግ ያሉ የመገናኛ መንገዶችና መሰረተ ልማትን እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል። ሳፋሪኮም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹ ክፍያ የአሜሪካ ዶላር እና የኢትዮጵያ ብርን እንደሚጠቀም ገልጿል።
ይህን ተከትሎም የኔትዎርክ መጋራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮምን በሚያክል ትልቅ ድርጅት የሚቀርበውን አገልግሎት ለመወዳደር የሚያስችል ስልታዊ መፍትሄ ነው ሲል ሳፋሪኮም መግለፁን ዘ ኢስት አፍሪካን ሚዲያ ዘግቧል።
በተያያዘ ሳፋሪኮም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማሳለጥ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገነቡትን የኮንክሪት ምስሶዎች እንደሚጠቀም እና አዳዲስ ምስሶዎች እንደማይገነባ ገልጿል።
ሳፋሪኮም እና ኢትዮ የቴሌኮም የቴሌኮም ማማዎችን ጨምሮ አንዳንድ መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለመጠቀም በመርህ ደረጃ መስማማታቸው መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን፣ የሳፋሪኮም ደንበኞች በመላ አገሪቱ የስልክ ኔትዎርክ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ስምምነቱ ተግባራዊ ሳይሆን ሳፋሪኮም ቀድሞ አገልግሎቱን ከጀመረ ግን፣ የሳፋሪኮም ደንበኞች ስልክ መደዋወል የሚችሉት እርስ በእርስ ብቻ እንደሆነ መነገሩም ይታወቃል።