ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ቀናት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በአሻባሪነት በተሰየመው የኦነግ ሸኔ ኃይሎች በተቀሰቀሰ ግጭት፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የፀጥታ ኃይሎችና ንፁኃን ዜጎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለጹት፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ ሞላሌ ቀበሌ በሸዋሮቢት ቀወት ወረዳ ጀጀባ ቀበሌ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ብሔረሰብ ዞን ጂሌ ጥሙጋ አካባቢዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በዜጎች ላይ ግድያ፣ የመቁሰል አደጋና ከቤትና መኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል፡፡
በተለይም በኦሮሞ ብሔረሰብ በጅሌ ጥሙጋ በኩል አልፈው በመጡት የኦነግ ሸኔና መሰል ኃይሎች የተፈጸመው ጥቃት አደገኛ እንደነበር የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ ይህን ኃይል ለመከላከል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸውን ያጡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡