ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የማዕድን ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን 83 በመቶ ድርሻ የተመሠረተው የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር በአፋር ክልል አፍዴራ የተሰጠው የጨው ማምረት ፈቃድ እንዳይታደስ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ጠየቀ።
ጥያቄውን ያቀረቡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አወል አርባ እንደሆኑ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አወል ጥያቄውን ያቀረቡት ለማዕድን ሚኒስቴር መሆኑን የገለጹት ምንጮች የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ላለፉት ሃያ ዓመታት በአፋር ክልል ጨው ለማምረት ሲጠቀምበት የነበረው የማዕድን ፈቃድ በመጪው ሰኔ 2014 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ በማመልከት፣ የማዕድን ሚኒስቴር የማኅበሩን ፈቃድ ለተጨማሪ ጊዜ እንዳያድስ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ለአክስሲዮን ማኅበሩ የተሰጠው የማዕድን ፈቃድ ጊዜ ሲጠናቀቅ ይዞታው ለክልሉ እንዲመለስ፣ በይዞታው ላይ ጨው የማምረት አዲስ የማዕድን ፈቃድ ለአፋር ልማት ድርጅት እንዲሰጥ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን በአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ላይ 83 በመቶ ድርሻ በመያዝ ወሳኝ ባለድርሻ ሲሆን፣ ቀሪው 17 በመቶ የሕወሓት ኢንዶውመንት የሆነው ኢፈርትና ሌሎች ባለድርሻዎች የተያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።