ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ትላንት በጎንደር ከተማ የተካሄደው ቀድሞ የታቀደበት ጭፍጨፋ ነው ሲል ገለፀ። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት በበኩሉ በጎንደር የተፈፀመው ጭፍጨፋ እና የሽብር ጥቃት ነው ሲል ገለፀ።
ምክር ቤቶቹ የሸይኽ ከማል ለጋስ የቀብር ስነ ስርአት እንደ መንስኤ በመጠቀም ቀድሞ በታቀደ መልኩ በሙስሊሙ ላይ በተፈፀመውን ጭፍጨፋ፣ የ21 ሰዎች በግፍ መገደላቸውን እና መስጂዶችና ቁርአን መቃጠሉን ገልጿል።
በሙስሊሙ ላይ የተቃጣን አጥፊ የሆነና በፅንፈኞች ወገን ቀድሞ የተቀነባበረን ግልፅ የሆነ የወንጀል ድርጊት የክልሉ ሚዲያዎች፣ መንግስት እና አንዳንድ የፖለቲካ ፓሪቲዎች በጉዳዩ ላይ የሰጡት መግለጫ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት የማይመጥን ነው ሲል ምክር ቤቱ ገልጿል።
እነዚሁ አካላት በመስሊሙ ላይ የተቃጣውንና የ21 ሙስሊሞችን ህይወት የቀጠፈውን ወንጀል የእርስ በርስ ግጭትና በሀሰት በድንበር ምክንያት የተፈጠረ ነው በማለት ያወጡት መግለጫ ሀገርን ለማፈራረስ ላቀዱ ሰዎች ሽፋን ከመሆኑም ባሻገር ምክር ቤታችንንም ሆነ ህዝበ ሙስሊሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳዝኗል ሲል አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበር በበኩሉ ትላንት ምሽት በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስት የሀገርን እና የህዝቡን ደህንነት በተቀናጀ ሁኔታ እንዲያስጠብቅ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ አሳሰበ።
በሼኽ ኤልያስ ጥንታዊ የሙስሊም መካነመቃብር ላይ ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በጎንደር ከተማ የሰው ህይወት ማለፉ ጉዳትም መደረሱን ይታወቃል።