ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የክልሉ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ትላንት ሚያዝያ 20/2014 ዓ/ም በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ እና በሳንኩራ ወረዳ ላይ በሀይማኖት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ገልጿል።
ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃት የክልሉ መንግስት አይታገስም ያለው መግለጫው በስልጤ ዞን የተጀመረው ጥቃት ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይዛመት ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርበታል ብሏል።
የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የጠቀሰው መግለጫው በሀይማኖት ተቋማት እና በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላትንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች ላይ አስፈላጊውን ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ብሏል። ትናንት በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ሙስሊም ጽንፈኞች በቅዱስ ሩፋዔል እና ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ሲል የሐድያ እና ስልጤ አገረ ስብከት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በጻፈው ደብዳቤ ማስታወቁን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች መዘገባቸው ይታወቃል ጽንፈኛ የተባሉት ወደ ቤተ ክርስቲያናት በኃይል በመግባት በካህናቱ ላይ ጥቃት እንደፈጸሙ እና ቤተ ክርስቲያን እንዳቃጠሉ አገረ ስብከቱ ገልጿል ። ጽንፈኞቹ ቤተ ክርስቲያን ካቃጠሉ በኋላ በከተማዋ የክርስቲያኖችን ሆቴሎች እየለዩ ጉዳት አድርሰዋል ብሏል።