ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ከህግ አግባብ ውጪ ታስረዋል ያላቸውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራሮች እንዲፈቱ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በነፃ የተሰናበቱ ምንም አይነት ክስ ያልተመሰረተባቸው እና ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደማይመሰርትባቸው ተረጋግጦ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ነገር ግን ከወራት እስከ 2 ዓመት ለሚሆን ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙና የተወሰኑትም በእስሩ ሂደት በተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እና ድብደባ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና የጤና እክል የተጋለጡ እስረኞች ናቸው ብሏል።
የኢሰመኮ የሲቪል ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል “በተለይም ታሳሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በሕዝባዊ አገልግሎት ስራቸው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይጋለጡ ጥበቃ ሊደረግ ሲገባ፤ በተግባር የተገላቢጦሽ መሆኑ አሳዛኝ በመሆኑ ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት ያስፈልገዋል” ሲሉ አሳስበዋል።
የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ የሚገባ ሲሆን በተጨማሪም የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በተደጋጋሚ ካደረጋቸው ክትትሎች በተጨማሪ ከመጋቢት 1 እስከ 10 2014 ዓ.ም. ድረስ በሶስት የፖሊስ መምሪያዎች በአካል በመገኘት እስረኞችን እና የፖሊስ አባላትን ማናገሩን ገልጿል።
ክትትል የተደረገባቸው የቡራዩ ከተማ፣ የገላን ከተማ እና የሰበታ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ሲሆኑ በእነዚህና ሌሎች ማዕከላት 9 የኦነግ አመራሮች መታሰራቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል።