ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ትላንት ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱት የመገናኛ በዙኀን ባለሙያዎቹ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ክሳቸው ተሰማ።

የፍትሕ መፅሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በህዝብ ዘንድ አመኔታ ለማሳጣትና ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል መጠርጠሩን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገልጿል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ መከላከያን መተቸት እምነት ማሳጣት አይደለም ሲል ተከራክሯል። ፖሊስ በዩቱዩብ ቃለመጠይቅ እያደረገ ከሌሎች አካላት ጋር ሁከትና አመጽ የማነሳሳት ስራ እየሰሩ ነው ሲል ባቀረበው የመነሻ ምርመራ ሪፖርትን በተመለከተ ጋዜጠኛ ተመስገን ከ4 አመት ወዲህ ምንም አይነት ከማንም ጋር ቃለመጠየቅ እንዳላደረገ ጠበቃ ሄኖክ አብራርቷል።

ጠበቃው እንደገለፀው ፖሊስ የጋዜጠኛውን መኖሪያ ቤትና መስሪያ ቤት በመፈተሽ የሚፈልጉትን ማስረጃ በመውሰዳቸው እንዲሁም ተመስገን ደሳለኝ ከሀገር የሚወጣ ባለመሆኑ የዋስትና መብቱ እንዲከበር የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተያያዘ ዜና መርማሪ ፖሊስ የ’ኢትዮ ፎረም’ ሚድያ አዘጋጅ የሆነው ያየሰው ሽመልስ በሀገሪቷ የስውር ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት እንዲሁም የሚዲያ ጦርነት ከከፈቱ የተደራጁ አካላት እንዳሉ ገልጾ “የሚዲያ ጦርነት ከፍተው ብሔርን ከብሔር እና ሀይማኖትን ከሀይማኖት እንዲጋጭ የፌደራል መንግስት እና ህዝብ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ሚዲያን በመጠቀም ከሚሰሩ ሰዎች መካከል አንዱ እሱ ነው” በማለት አስረድቷል።

ተጠርጣሪ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ “ፖሊስ ይዤዋለው ካለኝ በየትኛው ሚዲያ መቼ ምን የሚለውን በግልጽ አማረኛ ሊያቀርብ ይገባ ነበር ነገር ግን አላቀረበም ፊደል እንደቆጠረ ሰው ሲታይ የሚዲያ ስራ የተደበቀ አይደለም” ሲል ገልጿል። “ከዚህ በፊትም ስራዬን እንዳልሰራ እያስፈራሩኝ ስራ አቁሜያለው በህዝብ ላይ አሳመጸ ከተባለም በህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ሊቀርብ ይገባ ነበር ነገር ግን አልቀረበም” ብሏል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መታሰሩንና እንዳልተፈረደበት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ፖሊስ በበኩሉ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ የ14 ቀን ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 29 ቀን የ10 ቀናት ጊዜ መፍቀዱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

LEAVE A REPLY