መልካም እረፍት ይሁንልሽ!
በ1966 ዓ/ም በሰሜን ኢትዮጵያ߹ በተለይም በወሎ ጠቅላይ ግዛት አስከፊ ረሃብ ነበር፡፡ ችጋሩ በአጭር ጊዜ የብዙ ህዝብን ህይወት ቀጠፈ፡፡ በረሃብ የጠወለገ ህዝብ፣ ከሞት ጋር የተፋጠጠ ማህበረሰብ፣ ከአስከሬን ጋር የተላመደ ትውልድ
ነበር፡፡
ወሎዬዋ ቆንጆ በዚያ ዓመት ነበር የተወለደችው፡፡ በረሃቡ ዘመን ጨቅላ ህፃን ነበረች፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ተአምር እኩዮቿ ሁሉ ሲያልቁ እሷ ተረፈች፡፡
የማያልፍ የለም ያ የረሃብ ዘመን አለፈ፡፡ እህቴዋ አደገች፣ ትምህርት
ቤትም ገባች፡፡
በ 1977 ዓ/ም ወሎዬዋ ቆንጆ የ11 ዓመት ታዳጊ ሆና ሳለ እንደገና ረሃብ ወደ ወሎ መጣ፡፡ እጅግ አስከፊ ነበር! እርሷም ቤተሰቧም ዳግም ተራቡ፡፡
በጊዜው የነበረው የደርግ መንግስት መፍትሄ ነው ብሎ ያሰበውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡
ወሎዬዋ ቆንጆ እስከ ቤተሰቧ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተወሰደች፡፡
ደስ አላት! ያው
ሃገሯ አይደል???
እናም ወሎዬዋ ቆንጆ በደስታ አደገች፣ አጎጠጎጠች፣ ትምህርቷን
ቀጠለች፣ አዲስ ቋንቋም ተማረች፡፡ እድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ሲደርስ እህቴዋ
ተዳረች… አገባች… ሁለት ልጆች ወለደች፡፡
ወሎዬዋ ቆንጆ በዚህ በያዝነው ዓመት 48 ዓመት ደፍናለች፡፡ ልጆቿ
እያደጉላት ነበር፡፡ ብዙ ህልም ነበራት፡፡ ግን ምን ያደርጋል በተረገመች ቀን በድንገት
ቤቷ በታጣቂዎች ተወረረ፡፡ በጣም ደነገጠች! ምንም አላጠፋችም! ማንንም
አልበደለችም!
ታጣቂዎቹ በመጀመርያ ያይን ማረፊያዋ፣ ተስፋዋ፣ ዓለሟ የሆኑ
ልጆቿን ፊት ለፊቷ በስለት አረዷቸው፡፡
ከዚያም ወሎዬዋ ቆንጆ የተኩስ እሩምታ
ተከፈተባት! በደም ተለውሳ ተዘረረች፡፡ ከውጪ የድሃ ጎጆዋ ተዘጋ… እሳትም
ተለኮሰበት!… ኦሮማይ!
እጅግ የማከብረው የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ በረሃቡ ዘመን እንዲህ ብሎ
አዚሞ ነበር …
ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ
የረሃብን ጉንፋን ሲስሉ
እያዘንኩኝ ባይኔ Aይቼ
ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ! ”
እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ
“ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ
የሞት ጭንቀትን ሲስሉ
እያዘንኩኝ ባይኔ አይቼ
ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ! ”
አይዞሽ እህቴዋ! አይዞሽ እህት ዓለም! ፈጣሪ በሰማይ ላንቺና ለልጆችሽ ቦታ
አለው፡፡ እዚያ መጤ አትባይም፣ አትሰደጂም፣ አትጨነቂም፡፡ አይዞሽ እህቴዋ! በዚያ
ረሃብ የለም፣ ተኩስ የለም፣ ገጀራ የለም፣ ፍርሃት የለም፡፡ አትስጊ እህቴዋ! እዚያኮ
እንደ ምድር አይደለም! በዚያ ፍትህ አለ፣ ሰላም አለ፣ እረፍት አለ፡፡
አትፍሪ እህት ዓለም! በዚያ የዓምላክሽን ፍቅር ታያለሽ፣ እምባሽ ይታበሳል፣ ልጆችሽም ደስ ይላቸዋል፡፡ አይዞሽ እህቴዋ!
ወሎዬዋ ቆንጆ፣ ደግዋ እህቴዋ፣ ደህና ሁኚ!
መልካም እረፍት ይሁንልሽ !
የሚወድሽ፣ የሚናፍቅሽ ወንድምሽ
ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ