ሩጫዬን አቁሜያለሁ || ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ስራ ማቆሙን ገለጸ

ሩጫዬን አቁሜያለሁ || ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ስራ ማቆሙን ገለጸ

ከባድ ውሳኔ ነው። በህይወት ዘመኔ እንዲህ ዓይነት የነፍስ ትንቅንቅ የሚጠይቅ ውሳኔ ላይ የደረስኩበት አጋጣሚ የለም። ወደፊትም ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። አሁን ግን ከባዱን ውሳኔ ወስኛለሁ። ከዚያ በፊት ከራሴ ጋር ዝግ ስብሰባ በተደጋጋሚ አድርጌአለሁ። ከነፍሴ ጋር ተሟግቼአለሁ። የሚቀርቡኝን ወዳጆች አማክሬአለሁ። በመጨረሻም መሆን ይኖርበታል ያልኩትን አድርጌአለሁ። ምርጫ የለኝም።

አዎን! ማይክና ብዕር ሰቅዬአለሁ። ከእንግዲህ በየትኛውም የሚዲያ መድረክ ላይ አልገኝም። ከምሰራበት EMS መልቀቄን የማሳውቀው በከባድ ሀዘን ነው። ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩኝም የቤተሰቤ ጉዳይ ግን ዋንኛው መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ። ከአራቱ የስንብት ምክንያቶች ሶስቱ ከእኔና ከቤተሰቤ ጋር የተያያዙ ናቸው። ባለፉት 16ዓመታት፣ ከሀገር ቤት አንስቶ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ አብራችሁኝ የነበራችሁ፣ በዚህም በዚያም ጩኸት ስንጋራ በጋራ የነበርን ሁሉ ከልብ አመሰግናችኋለሁ።

ባልደረቦቼ በርቱ። በEMS በጋራ የጀመርነውን ራዕይ ከዳር እንደምታደርሱት ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። አብሬአችሁ እስከ ደሴቲቱ ባለመዝለቄ አዝናለሁ። የተጀመረው መንገድ አባጣ ጎርባጣ ቢበዛውም በኢትዮጵያዊ ጽናት እንደምትሻገሩት እተማመንባችኋለሁ። አንድ ቀን ዳግም እቀላቀላችሁ ይሆናል። ለጊዜው እኔ ሩጫዬን አቁሜአለሁ። እናንተ ግን ጠንክሩ። ግፉበት። ኢትዮጵያ ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለችና።

ለሁሉም ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቅልን። ከመጣባት ክፉ አደጋ ይታደጋት ዘንድ ጸሎቴን እቀጥላለሁ። በጥሞና ጊዜዬም ስለኢትዮጵያ ማሰቤን አላቋርጥም። ሀገሬ ልቤ ውስጥ ናትና ሁሌም፣ የትም አስባታለሁ። በተረፈ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች። ቸር ሰንብቱ!

LEAVE A REPLY