ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሚኖርበት አትላንታ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ያቀናው ተወዳጁና አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ የህመም ምልክት ሳይታይበት ከሚኖርበት ከአትላንታ ተነስቶ አዲስ አበባ በገባ በአምተኛ ቀኑ ማረፉ ተሰምቷል።
ለበርካታ ጊዜያት በኢህአደግ ደህንነቶች በግፍ ታስሯል ተደብድቧል፣ ከሀገር ተሳዷል። ለጥቂት ጊዜ ካናዳ ወደ 20 አመታት ደግሞ በአሜሪካን ሀገር አትላንታ ግዛት ኖሯል። የትንሣኤ ራዲዮ መስራችና የመለስ ዜናዊንና የባለቤታቸውን የወ/ሮ አዜብን ጨምሮ የህወሀት ባለስልጣናት ከህዝብ ዘርፈው በውጭ ሀገር ባንኮች ያስቀመጡትን ገንዘብ በማጋለጥ፤ እሰከ አሜሪካን ፍርድ ቤት የደረሰውን የነመለስ ዜናዊን ክስ ደግሞ ከባልደረቦቹ ጋር በማሸነፍ ሲታወስ ይኖራል።
ዳዊት የኢትዮጵያ ታሪክን በመፃፍና በታሪክ ዙሪያ ሽንጡን ገትሮ መከራከር የሚችል የታሪክ አዋቂም ነበር። ደዊት በስደት በተለይ በኬንያ፣ ዩጋነዳ፣ ሱዳንና የመን ይኖሩ የነበሩ ጋዜጠኞች እንዲረዱ ብዙ ደክሟል። ዳዊት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ሰብሳቢ፣ ተሟጋች፣ ግንባር ቀደም ተፋላሚም ነበር።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ የተወለደው በአዲስ አበባ ቄራ አካባቢ፤ ልዩ ስሙ ኬላ በር የሚባለው ሠፈር ታህሳስ 19 ቀን 1961 ዓ.ም እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።
ተወዳጁና ሰው አክባሪው አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በሃገር ቤት እያለ በሚያሳትመው ፊያሜታ ጋዜጣ የሚታውቀ ሲሆን፤ በለገዳዲ ሬዲዮ፣ በአሜሪካ አገር ደግሞ በትንሳኤ እና በአድማስ ሬዲዮ፣ እንዲሁም ድንቅ መጽሔት በመሥራትና በመመስረት ይታወቃል።
አንጋፋውና ተወዳጁ ጋዜጠኛ የዳዊት ከበደ ወየሳ ማረፍ በርካታ የቀድሞ የሙያ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ የሰራቸው ትላለልቅ ስራዎቹ በማውሳት በማህበራዊ ሚዲያ የተሰማቸው ጥልቅ ሀዘን እየገለፁ ይገኛሉ።
በተወዳጁ ጋዜጠኛ ዳዊት ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍል ለመላው ቤተሰቡ እና ወዳጆቹ መፅናትን ይመኛል።