በሃይማኖት ዙሪያ ያሉ ወቅታዊ ነገሮችን ስመለከት በዋናነት ችግሩ ራስን እንደ ፍጹም ንጹሕና እውነተኛ ቆጥሮ ሌላውን እንደ ኃጢአተኛና እንደ ሐሰተኛ ፈርጆ በአደባባይ መዝለፍ ኾኖ አገኘዋለሁ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድህነት፣ የጉስቁልና እና የመከራ ቀምበር የጫነች ቤተክርስቲያን አይደለችም።
ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ሲያልፍም ለአፍሪካውያን እኅትና ወንድሞች የሀገር ወዳድነት፣ የዕምነት ጽናት፣ የሰማዕትነት፣ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የሰላም እና የጥበብ ቀንዲል ናት። ጥንታዊነቷ ውስጥ እውነት፣ ጥበብ፣ ውበትን የተሞላ ወግና ሥርዓት አለ።
እርሷ ፊደል ቀርጻ፣ አስተርጉማ፣ ጠብቃ ያቆየችውን መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ አይደለም እርሷን በአደባባይ ለመዝለፍ፤ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትችትና ክርክር ለማድረግ ራሱ በቅድሚያ ለዋለችው ውለታ ተገቢውን አክብሮትና ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል።
በውስጧ ለክርስቶስ ካላቸው ፍቅር የተነሣ ዓለምን ትተው የመነኑ አባቶችን ይዛለች።
የቱም አባት ስለክርስቶስ እንጂ ስለሌላ አካል አልመነነም።
መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ በልቡናቸው ያተሙ የቀለም ቀንድ የተባሉ ሊቀ ሊቃውንት አሏት።
ይህቺን ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ልክ ክርስቶስንና ፍጡራንን ለይታ እንደማታውቅ፤ ልክ መጽሐፍ ቅዱስ አንብባ እንደማታውቅ አድርጎ መዝለፍ ቅጥ ያጣ ሞኝነት ነው።
የእርሷን መጻሕፍት ለመረዳት በእርሷ ነገረ ልቡና ውስጥ መኾን ያስፈልጋል።
መጻሕፍቷን የምትተረጉምበት መንገድ አላት። ቀርቦ ይህ ምን ማለት ነው? ብሎ በዝግታ መጠየቅ ተገቢ ነው። ቀርቦ አጥንቶ፣ መዝኖ በዕውቀት መተቻቸት፣ በሰከነ መንገድ ውይይት ማድረግ የአባት ነው።
ነገር ግን አንድ መሥመር ይዞ ብዙ ምዕመናን ያሉዋትን ቤተ ክርስቲያን እንደ ሀገር አደገኛ ኪሣራ ውስጥ ሊከት የሚችል ተራ ዘለፋ መሰንዘር ማንንም አርበኛ አያሰኝም።
አንዲት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያንንና ሃይማኖትን አጥንቶ ለመጨረስና ለማቃለል ቀርቶ በአንድ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪ ለማግኘት እንኳ ከ 5 ዓመት በላይ መማር ይጠይቃል።
ይልቁንም ጣትን ወደ ውጭ ከመጠቆም ቅድሚያ የራስን ጉድፍ ማጥራት ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው።
” (መክብብ 2፥14) እንዲል የሌላውን ቤት ከመተቸት በፊት የራስን ቤት መፈተሽ የአዋቂ ሰው እርምጃ ነው።
አንድ አገልጋይ ነኝ የሚል ሰው ያላበውን ላብ የተጠራረገበትን ሶፍት በልቼ ተፈወስኩ የሚል፤ የታኘከ ማስቲካ ለምዕመን ሰጥቶ እርሱን አኝኬ አረገዝኩ የሚል፤ አንድ ዕቃ ማጠቢያ ፎጣ ገዝቼ ተፈወስኩ፣ ዘይት በችርቻሮ ሽያጭ ገዝቼ ነገሬ ሁሉ ተለወጠ፣ የሃይላድ ውኃ በግዢ ጠጥቼ ተባረኩኝ የሚል ተረት ተረት ያለው በየት ቤተ ክርስቲያን ነው? የትኛው ሐዋርያ ወይስ ነቢይ ነው በካራቴ አጋንንት ያወጣው?
ስንፈልግ ስንፈልግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንወስዳለን። ሳንፈልግ ስንቀር መጽሐፍ ቅዱስ እንጠቅሳለን።
መጽሐፍ ቅዱስን የእኛን ሐሰት እውነት ለማድረግ የሌላውን እውነት ሐሰት ለማድረግ እየመረጥን የምንጠቅሰው መጽሐፍ ነው እንዴ? ከዚህ በላይ ኑፋቄ፣ ከዚህ በላይ ክህደት? ከዚህ በላይ ግለሰቦች የሚመለኩበት ቤተ ክርስቲያን አለ እንዴ? ለስንፈተ ወሲብ እክል ከ20-30 ደቂቃ ጨምሬያለሁ የሚል ዕብደት ከየት ይመጣል? ባልሠሩት ሀብት የመጎምዥት እና በምኞት ልክፍት መቃጠሉ የአደባባይ ነውረኝነት ነው።
የባንክ ደብተር ይዞ ገንዘብ ይጨመርልኛል እያለ በባዶ ተስፋ የሚንከረፈፍ ምዕመን የታየው በየት ነው?
በወንጌል እና በወንጌላዊያን ስም የተጧጧፈውን ሽቀላ፤ በወጣት እና በወጣቶች ስም የሚደረገውን ንግድ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ያነጣጠረ ኑፍቄ ወዘተ… ከቀን ወደ ቀን የሚታየው የሞራል ዝቅጠት ልብ የሚሰብር ነው።
ክርስትና ለሰው ልጆች ድኅነት የተከፈለን መሥዋዕትነት የሚፈክር ድንቅ ሃይማኖት ነው።
አሁን አሁን ግን ክርስትናን ሐሰተኛ አገልጋዮች የሰው ልጆችን ከእንስሳት ባነሰ መልኩ የሚበዘብዙበት መሣሪያ ኾኗል። እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ ክርስቶስ የሞተለትን ሰው ሐሰተኛ ፓስተሮች፣ ነቢያት ገደሉት።
ይህን በቃችሁ ቢለን መልካም ነበር።
ነገር ግን አገር እንዳይረጋጋ ወጣቶችን በሃይማኖት ስም ለብጥብጥ እና ለሁከት በሚያነሣሣ መንገድ ቁጣን መቀስቀስ ነውርም፣ ወንጀልም ነው። የሰላሙ ኢየሱስ መቼ ተሰብኮ አለቀና ነው? ፍቅርንና ሰላምን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ መቼ እንዲሠርፅ ተሰብኮ ነው መዘላለፉ?
የአንዱ ቤተ ክርስቲያን አማኝ የሌላውን ቤተ ዕምነት አማኝ ጉድፍ ሊያወጣ፣ ሊነቅስ ከመሞከሩ በፊት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ያስታውስ፦
“በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፦ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።” (ሉቃ 6፥ 41-42
ዩናስ ዘዉዴ ከበደ