በአባቴ ቀብር ላይ እናቴ ለምን አምራ ተዋበች ፣ አበባ ለምን መሰለች❓ ||...

በአባቴ ቀብር ላይ እናቴ ለምን አምራ ተዋበች ፣ አበባ ለምን መሰለች❓ || ቱካ ማቲዎስ

 

ነጭ ፀሐዳ ልብስ ለብሳ አማኑኤል ቤተክርስቲያን አውደምህረቱ ላይ ቁጭ ብላለች ፣ የሟቹ አባታችን የበርካታ አስተ ዓመታት ሚስቱ የሚወዳት እናታችን ። የምትወደው ቤተክርስቲያን ጥቁር ለብሳ አለመግባቷ ደስ አለኝ ፣ ይኽ እንዲኾን ያደረገው አባታችን ነው ፣ እንዴት እንደኾነ እነግራችኹ አለኹ።

ሰው የተገረመ ይመስላል ” ይኽ ሃዘን ነው ደስታ?” ፣ “ምን የሚሉት ባህል ነው ? ፣ ለቀብር ነጭ በነጭ ለብሶ አምሮ ተውቦ መምጣት?” ይኽንን እና ሌላም ሌላም ይላል ሰው።

የ ሰባት ወንዶች እና የ ስድስት ሴት ልጆች አባት ፣ የ ሃያ አንድ የልጅ ልጆች ሃያት እና የአራት የልጅ ልጅ ልጅ ልጆች ቅድመ ሃያትም የነበረው አባታችን ፣

እጅግ ጥንቁቅ ነበር ፣ የሚያስቀና ፣ ለምንም ነገር ዝግጁ ፣ ቀድሞ መገነዣውን ጨርቅ እና መታሰሪያውን ገመድ ገዝቷል። ቀድሞ ስለሞቱ ሲናገር ብዙዎቻችን አላመነውም እንጂ ለኔም በግሌ ፣ለሌሎች ልጆቹም ተናግሯል ።

“ማቴዎስ”
“አቤት ፣ አባዬ”
“መሄዴ ነው ባክኽ ፣ ይኽን ገና በዓል አላልፍም”
“እንዲኽ አይባልም ፣ ገና እኮ ነኽ! ፣ ለማን ጥለኽን ነው የት ምንትሄደው? በዓል እኮ ነው”
” ምንም ጥርጥር የለውም ይበቃኛል” አለኝ ።

እንባዬ ቢመጣም ፣ እንዳያየኝ ፊቴን አዙሬ በቁጣ አይነት እንደዛ እንደማይባል ነግሬው “ሰሞኑን ቡቡዬን (ልጄን) ይዤው እመጣለኹ አይዞኽ” ብዬው ወጣኹ።

ከልጄ ጋ ከቀናት በኃላ ስመጣ ፣ እያወሩ ልጄ ስሙን ከነ ቅድመ ሃያቱ ማለት እንደሚችል እየነገረው ፣

“ቡቡ ፣ ቶኤል ፣ ማቲዎስ ፣ ስራኒ ፣ ኬረታ ፣ በታ ፣ ገድሉ ፣ አቻሞ… ” ፣ ብሎ ሲጠፋበት “ሰንጋ በሬ ቂጡ በርበሬ” እያለ ሲጨምርበት አባቴ ከት ብሎ ሳቀ የአባቴ ሳቁ ያስቃል ፣ እየተሳሳቁ ነበር ደስ አለኝ ።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

ዛሬ አባቴን በሩን ዘግተው እየገነዙት “ካልገባኹ!” ብዬ አስቸግሬ ተከፍቶልኝ ገባኹ ፣ አባቴን አብሮ የኖሩት ጔደኞቹ ፣ ታናሽ ወንድሜ እና ዘመዶቹ ይገንዙታል ፣

“አቤት ንጽኽና አቤት ጽዳት” አለ የረዥም ጊዜ ጓደኛው ጋሽ ግርማ ደገፋ ፣ አባቴ ምስጢር ከኛ ለመደበቅ ከፈለገ ከዚኽ ጓደኛው ጋር ኦሮምኛ ቅልጥ አድርጎ “አካም ነጉማ ፣ ኔጌና በዳዳ ኦሊና አካም ማሎ…” እያለ ሲያወራ ይገርመኝ ነበር ።

አባቴ በሕይወት ሳለ ዋነኛ መርኹ “የሥጋ እና የነፍስ ንፅህና” ነበር ።

ጋሽ ጸጋዬ ቢደክማቸውም “ከመይ ጽቡቅ : ደዃን ደኹ” እያለ በትግርኛ የሚያወራቸው የክፉ ጊዜ ሸሻጊ ጓደኞቸውን በጥንቃቄ ይገንዛሉ ፣

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

አንድ ጊዜ አባቴ “ሰው ሞቷል በፍጥነት ይድረሱ” ተብሎ መልእክት ተነገረው ፣

“ና ተነስ እንሂድ” አለኝ ፣ ልጅ ነበርኩ ያኔ፣ ተከትዬው ከኋላው ሱክ ሱክ እያልኩ ሮጥኩ ፣ ከስፍራው ደረስን ቤቱ በሰዎች ተሞልቷል ፣

ስንደርስ “ጋሽ ስራኔ ፣ ጋሽ ስራኔ መጡ” ይላሉ የሰፈራችን ሰዎች “ከፈት ከፈት አድርጉላቸው” እኔን አንድ ሰው ወደውስጥ እንዳልገባ ከለከለኝ ፣
አባቴ ዘወር አለ “ና እንጂ” አለኝ በአይኔ መከልከሌን ነገርኩት እጄን ስቦ ወደውስጥ አስገባኝ ፣

ሟች በሰዎች ተከቦ ተጋድሟል ፣ አባቴ ሲመጣ መገነዝ ተጀመረ ፣ በባህር ዛፍ እና ግራዋ አጠቡት አስክሬኑን ፣ እጅ እግር አስተካከሉ የእግር አውራ ጣት በነጭ ነጠላ ጨርቅ አሰሩ ፣ እኔ የሚያደርጉትን በአግርሞት በአትኩሮት እያየኹ ነው።

ሲጨርሱ ወደቆምኩበት መጣ “ና እንሂድ ነገ ለሊት መነሳት አለብኝ ” አለኝ ወደቤት እየሄድን “ሰው እንዴት እንደሚገነዝ አየኽ ?” በሚገባ እንዳየኹ ነገርኩት።

ስለ ሕይወት እና ሞት በተግባር እያስተማረኝ ነበር።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

ዛሬም እኔ ሦስት አመት ከአራት ወር ለኾነው ለኔ ልጅ ሃያቱ እንደሞተ በግልጽ ነገርኩት ፣
(ከዚኽ በፊት ትንሹ ውሻ ሞታበት መገነዝ አስተምሬው አብረን ቆመን ቆፍረን ጸሎት አድርገን ቀብረናታል ስለዚኽ የሞት ጽንሠ ሃሳብን ተረድቷል)

ዛሬም ልጄ ከቤተሰባችን እና ከዘመድ አዝማዶቻችን በሃያቱ ቀብር የተገኘ በእድሜ ትንሹ ኾኗል ፣ (ሰው ቢከለክልም “ይኺድ ይይ” ብዬ ከእናቱ ጋ ወደቀብር ሄደ)

“ሃያትኽ ምን ኾኖ ነው? ” ሲባል
“ሞቶ” ይላል
“ምን አድርገነው መጣን” ተብሎ ሲጠየቅ
“ቀብረነው ፣ ወደ ሰማይ እግዣቤል ጋል አድርሰነው” ይላል ልጄ ።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

አባቴ ሞቱ ታውቆት ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ነበር ፣
“ሰው እንዳታስቸግሩ” ይል ነበር አብዝቶ ፣

በአካለ ሥጋ እያለ ከማረፉ በፊት የዋኋ ፣ እንደ እርግብ ንፁዃ ፣ ደጓ እና ብዙ አብራ ላሳለፈችው ለልጆቹ እናት
“ያጎደልሽብኝ የለምና አትዘኚ” ሲላት ፣ ሲሞት ነጭ በነጭ እንድትለብስ አስጠንቅቆ ፣ ልጆቹ ሀዘን ሳያበዙ ፣ የልጅ ልጆቹ ፣ ዘመድ አዝማዶቹ ፣ ጓደኞቹ ፣ የአካባቢውን ሰዎች ወጣቶችን ህፃናትን ኹሉ መርቆ ፣ ምስጋና አቅርቦ እራሳቸው ላይ በደንቡ መሰረት ነጭ ሻሽ እንዲያስሩ ፣ ወንዱም ሴቱም ቂቤ እንዲቀቡ ፣ አዝዞና ተናዞ ነው ያረፈው።

በእውነት አባቴ ስለኾነ ሳይኾን ሃገር ቀዬው የሚመሰክርለት መልካም ሰው ነበር ፣ ሙስሊሙ ክርስቲያኑ “እሪሪ…” ብሎ ቀበረው ፣
ወጣቱ ጉልበቱን ሳይሰስት እያስተናበረ ፣ አቅመ ደካሞች አዛውንቶች እያለቀሱ በእግራቸው በሸክምም ጭምር ተጉዘው ቀበሩት ።

የሚወዳት የሃገሩ ኢትዮጵያ ሰዎች አከበሩት ፣ እግዚ”‘አብ”‘ሔር ያክብራቸው።
ለካ ከጸሎታት መካከል “አሟሟቴን አሳምርልኝ” የሚሉት መልካም ጸሎት ነው።

፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲

“መርፌ መጣያኮ ጠፋ” ብሎ ሰው እስኪገረም ሰው በዛ ፣ ፀበል ፃዲቁም ተትረፈረፈ ፣ አባቴ ማህበራዊነት – ማህበረ-ሰብዓዊነት ምን ያኽል ጠቃሚ እንደኾነ በሕይወቱ በሞቱም ሰብኮ ኼደ ።

አንድ ሰው ወደኔ መጣና የቀብሩ ዕለት
“የአበባ ጉንጉኑስ? አለኝ
” እበባ ጉንጉን አያስፈልግም!” አልኩት ” ያቹት እዛ ማዶ አበባ መስላ ያለችው ባልተ-ቤቱ እሷናት አበባው ጉንጉኑ”

{እናቴ ስሟ ጌጤነሽ ቢኾንም የሰፈር ሰው “አበባ” ይላታል ፣ አካሏ ባህሪዋ ፀባይዋ አበባ ነው ሲል}}

ለእናቴ እድሜና ጤና እየተመኘኹ ፣ የአባቴን ነፍሱን ከደጋጎች ጎን ያሳርፈው ።

ኹላችኹንም አመሰግናለኹ ፣ የኾነው እንዳለ ኾኖ ሰዎች ኹሉ መልካሞች ናቸው።

LEAVE A REPLY