ነገ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ይከበራል፤ ጥምቀት ይከተላል፤ እኒህን ትልልቅ በዓላት የሚከሩበትን ቀናት የደነገገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት፤ ስለእርሱዋ የሚሰማኝን ለመናገር ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ የማገኝ አይመስለኝም፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የኢትዮጵያ ቀዳሚ አንደበት ናት ፤ የግእዝ ፊደል የተወለደው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአክሱም ነው፤ ይሁን እንጂ ፊደሉን ከርክመው፥ አሰማምረው ፥ ልገው ፥ ስርአት አስይዘው የዛሬውን መልክ ያስያዙት የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሊቃውንት ናቸው፤ በአማርኛ በተራቀቅሁ ቁጥር የኒህን ሊቃውንት ውለታ አልዘነጋም::
የሰውን ልጅ ከበሬ ወይም ከጉማሬ የሚለየው ባህል ነው፤ በአእምሮ የማይራቀቅ ባህል መፍጠር አይቸልም፤ ኢትዮጵያ ለእንግዳ በኩራት ከምታሳያቸው ደማቅ እና አይነተኛ (ኦሪጂናል) የባህል መለዮዎች መካከል አብዛኞቹ የመነጩት ከአድባራት ነው፤ እድሜ ይስጠኝ እንጂ ዝርዝሩን እያረፍሁ አወጋዋለሁ::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ባንድ ጊዜ የባህል ሚዝየም እና የባህል መድረክ መሆን ትችላለች፤ በፈርኦኖች ዘመን የኖረ ጽናጽል ብሪቲሽ ሚይዘይም ውስጥ ማግኘት ትችላለህ፤ ጽናጽሉ ወደ ዜማ ሲተረጎም ለመታዘብ ግን አብማ ማርያም ቤተክርስትያን መገኘት ያስፈልጋል::
የቤተክርስትያን ቅዳሴ መታደም ዝም ብሎ የአማኞችን ጉባኤ እንደመታደም አይደለም፤ የጊዜ መኪና እንደመሳፈር ነው፤ በሀያ አንደኛው ክፍለዘመንን ለቅቀህ ራስህን በመካከለኛው ዘመን ውስጥ ታገኘዋለህ፤ አጼ ናኦድ ያደመጡትን ዜማ መስማት መቻልህ ካላስደነቀህ ምን ሊያስደንቅህ ይችላል? ምንጅላቶችህ ያሸተቱትን እጣን ወይም ከሴ ማሽተት መቻልህ ካላስገረመህ ምን ሊያስገርምህ ይችላል? እኔ እንዲህ አይነቱን እድል ጊዜን እንደማስገበር እቆጥረዋለሁ::
የብሉይን መጽሀፍት ብታነቢ የጥንታዊ እብራውያን ታሪክ፤ ባህል እና ህልም ታውቂያለሽ፤ ሀዲስ ኪዳንን ስታጠኚ የጥንት እብራውያን ግሪካውያን እና ሮማውያን እምነት፤ ህልም እና ስነልቦና ትገነዘቢያለሽ፤ የቀደምት አባቶችሽ እና እናቶችሽ ምን ያስቡ እንደነበር ለመረዳት ከፈለግሽ ግን የጻድቃን ገድላትን ማንበብ ይጠበቅብሻል፤ የኢትዮጵያውያንን ስነጽሁፍ፥ ስነልቦና ፥ መልክአምድር ለማወቅ የሚገደው ሰው የጻድቃን ገድላትን እና ድርሳናትን መመርመር ይጠበቅበታል::
በአርባ ቀኔ ማንኩሳ ሚካኤል ተጠምቂያለሁ፤ የልደት ስሜም ወልደሚካኤል መሆኑ ይታወቅልኝ! በባህል ረገድ ራሴን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እመድባለሁ፤ ያም ሆኖ ዓለማዊነቴን ለመሸመጥጥ አልሞክርም፤ ሊቁ አድማሱ ጀምበሬ “ የምናውቀውን ዓለም በማናውቀው ዓለም እንለውጣለን” ይላሉ፤ ይመቻቸው! እኔ የሚታወቀውን ዓለም በማይታወቀው ዓለም የሚያስለውጥ ምክንያት እስካሁን አልገጠመኝም፤ የሚታወቀውን ዓለም ከነ ትርኪምርኪው በጸጋ እጄን ዘርግቼ፥ ልቦናየን ከፍቼ እቀበላለሁ:: በምድር ስኖር የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የስልጣኔ ፍሬዎችን ያበረከቱልን ሁሉ ማክበር እና ማመስገን እንደሚገባን ተረድቻለሁ::
ሰናይ በአል!