የአብይ የጎርጎራው ጉዞ || መሳይ መኮነን

የአብይ የጎርጎራው ጉዞ || መሳይ መኮነን

የአብይ የጎርጎራው ጉዞ ሽፋን ናት። ዓላማው የኦሮሚያ ብልጽግናን የእውር ድንብር ሽምጥ ግልቢያ አሜን ብላችሁ ተቀበሉ ዓይነት መዳረሻው የሆነ ጥብቅ ውይይት ለማድረግ ነው። ሰውዬው የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ውስጥ ዘው ብሎ ገብተው እየተንቦራጨቁ ነው። በመላው ኦሮሚያ ሰልፍ አስወጥተው እሳቸው ባህር ዳር ላይ ”እንግዲህ በኦሮሞ ዓይን ከመጣችሁ ጫፌን መንካት ትችላላችሁ። እኔ ተነካሁ ማለት ይህ የምታዩት ማዕበል ፋሲል ቤተመንግስት ለመድረስ 24 ሰዓት አይፈጅበትም” የምትል ፍርሃት ወለድ ማስፈራሪያ ለማሰማት ተዘጋጅተዋል። እያበቃ ያለው ሳምንት የሰውዬውን እውነተኛ ቀለም ከምን ጊዜውም በላይ ፍንትው አድርጎ አውጥቷል። ጭምብላቸው ወልቆ የተደበቀው ማንነታቸው ዕርቃኑን አደባባይ ላይ ተሰጥቷል። በተለይ ”እኛ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን አናፈርስም። ማፍረስ ከፈለግን ደግሞ የሚያቆመን ሃይል የለም” የሚል ንግግር በፓርላማ ካሰሙ በኋላ አንደኛውን በስብሰናል፡ ዶፍ በሆነ ዝናብ ውስጥም መራመድ እንችላለን እያሉ ናቸው።

እነጌታቸው ረዳ ያልተቀደሰው ጋብቻ ላይ ከታደሙና ጫጉላ ሽርሽሯንም ከአቶ ሽመልስ ጋር ካሳለፉ በኋላ ወደ መቀሌ ተመለሰዋል። በዚህ ሳምንት የሁለት ዓመቷን በጀት ከድጎማዋ ጋር ይልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠ/ሚሩ ባህርዳር ላይ የአማራ አመራሮችን በስብሰባ ሲጠምዱ የእሳቸው የነፍስ አጋር፡ የሚስጢራዊ ፕሮጀክቶች ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ደግሞ ከህወሀት ጋር የተጀመረውን ልዩ ግንኙነት መልክ በማስያዝ ላይ እረፍት አጥተው ሰንብተዋል። የባህርዳሩም ሆነ የአዲስ አበባው የሁለቱ የኦሮሚያ ብልጽግና መሪዎች ዓላማ ከዚህ በፊት እንደነበረው ኮንቪንስ ወይም ኮንፊውዝ አይደለም። ዓይን ያወጣ የበላይነት ጥማችንን ከዳር ለማድረስ በጀመርነው ጎዳና ላይ እንቅፋት አትሁኑብን የሚል ግብና ተልዕኮ ያለው ነው። እንቅፋት ከሆናችሁ ሀገሪቱን ”ዝናብ ያበላሸው ሰርግ” እናስመስላታለን የምትልም ማስፈራሪያ ታክሎበታል።

ጠ/ሚሩ ጓዛቸውን ጠቅልለው የጎሳ ፖሊቲካ ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል። ሰሞኑን ‘ምን ታመጣላችሁ’ ብለው በአደባባይ ስለማን እስከቀራኒዮ ድረስ እንደሚዋደቁ በግልጽ ነግረውናል። ከዚህ በኋላ እሳቸውን የኢትዮጵያ ዋስና ጠበቃ አድርጎ የሚያምን ሰው ካለ ጤንነቱን በጊዜ ይፈትሽ። የነገውን ሰልፍ ሲያስጠሩ ዓላማው ግልጽ ነው። እኔ የምሞትለትና ለእኔ የሚሞትልኝ ብሄር አለኝ ነው መልዕክቱ። በበቀደሙ የፓርላማ ውሏአቸው ‘ስልጣን ልቀቅ’ ተባልኩኝ ብለው በንዴት ጦፈው፡ እጅግ አሳፋሪ የሆነ የፊዚክስ (እሳቸው የማቲማቲክስ ቢሉትም’) ቲዮሪ አንስተው ፡የብሄር ካርድ በመምዘዝ ሲጫወቱ ቀጣዩ አካሄዳቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም ነበር።

ሰውዬው አሁን ፍጥነት ላይ ናቸው። ፍሬን የበጠሰ መኪና ሆነዋል። በግንድም፡ በድንጋይም፡ ብቻ በሆነ ሃይል ማስቆም ካልተቻለ በዚህ ፍጥነታቸው የሚያደርሱት ጉዳት በቀላሉ የሚቀለበስ ላይሆን ይችላል። ችኩልነት + ሴራ + ጥራዝ ነጠቅ እውቀት + ዘረኝነት + የአቅም ማነስ + ስልጣን ተደማምረው ተነስተዋል። ፊት ለፊት ያገኘውን ሁሉ እየጠረማመሰ ነው። ገደሉ ሩቅ አይደለም። ፍሬን የበጠሰው መኪና ግስጋሴው ወደዚያው ነው። በቶሎ የምናስቆመው እንዴት ነው? የሚለው አብዝቶ የሚያስጨንቀን፡ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

LEAVE A REPLY