ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ህገወጥ የጵጵስና ሹመት ፈጽመዋል የተባሉ አካላት የቤተክርስትያን ንብረቶችን በማሸሸና ንዋየ ቅዱሳትን በመሸጥ ላይ ናቸው ተባለ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገወጥ የጳጳሳት ሹመት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠቀሱ አካላት አሁንም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ አገረ ስብከት ተገቢ ያልሆነ ተግባር እየፈጸሙ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአገር ውስጥ ሚዲያ ተናግሯል፡፡
ነዋሪዎች አክለውም ለሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ አግልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን በከብት መድለቢያ የደለቡ ሰንጋዎችን እንዲሁም የተለያዩ ንብረቶችን በማሸሽ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ለአብነትም በጭሮ ከተማ ከሚገኙ አምስት አብያተክርስትያናት ሦስቱን በኃይል ሰብረው በመግባት የተቆጣጠሩት እነዚህ አካላት በምዳዬ ምጽዋት ውስጥ የሚገኙ ገንዘቦችን በመውሰድ እና የአብያተ ክርስትያናቱን ንዋየቅዱሳት አውጥተው በመሸጥ ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም በአካባቢው የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች በቅዱስ ሲኖዶሱ ተለይተው በተወገዙ አካላት አንገለገልም በማለታቸው የቤተክርስትያን አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ይህን ተግባር እየፈጸሙ ያሉት አካላት እየታገዙ ያለው በመንግሥት የጸጥታ አካላት መሆኑን ጠቁመው፤ ድርጊታቸውን የሚቃወሙ አካላትን የማሰርና የማዋከብ ሥራ በመንግሥት አካላት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት ህግ እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ህገወጦችን ከማስቆም ይልቅ በተቃራኒው ጥያቄ ያቀረቡ አካላት ናቸው እስርና ወከባ እየተፈጸመባቸው ያለው ብለዋል፡፡
ስለሆነም በአካባቢው ያለው የመንግሥት መዋቅር ከቤተክርስትያን ላይ እጁን እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሚያና የብሔር ብሔረሰቦችን ሲኖዶስ እንመሰርታለን ያሉ አካላት ባለፈው ጥር ወር የ27 ኤጲስ ቆጶሳትን ሹመት ማከናወናቸው እና ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት እንደተላለፈባቸው ይታወቃል፡፡