መልዕክተ ቅዳሜ፤ መካር የሌለው … || ከበረራ በፊት አውሮፕላን ውስጥ የተከተበ

መልዕክተ ቅዳሜ፤ መካር የሌለው … || ከበረራ በፊት አውሮፕላን ውስጥ የተከተበ

ብልጽግና መሩ የአገዛዝ ሥርዓት መካር ያጣ ወይም ምክር የማይሰማ መሆኑን አንድ ሺ አንድ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ በቅርብ ሆኖ ላስተዋለ፣ በሕዝብ ውስጥ ያለውን ምሬት፣ ጉስቁልና እና ሰቆቃ ላጤነ፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚታየውን አይን ያወጣና ያፈጠጠ ሙስና (ፍቃድ ያገኘ ሌብነት ብለው ይቀለኛል)፣ እየተባባሰ የመጣውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው የጸጥታ ችግር፣ እየተዳፈነ የመጣው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸሙ አስከፊ የመብት ጥሰቶች፣ የመንግስት የጸጥታ ክፍሉ ከሕግ ማፈንገጥ (አክቲቪስት ኤርሚያስ መኩሪያ ታፍኖ በተሰወረ 13ኛ ቀኑ ፌደራል ፖሊስ ዘንድ መገኘቱ)፣ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ያለው የኑሮ ውድነትና (አንድ ኪሎ ቲማቲም 80ብር) እና የዋጋ ግሽፈት፣ ሚሊዬኖችን በልማት ስም ንብረታቸው ዘርፎ፣ ቤታቸውን አፍርሶ ሜዳ ላይ የሚጥል፣ ተደጋጋሚ የእስር ቤቶች መሰበርና የእስረኞች ማምለጥ እና ከሁለቱ አውራ ሃይማኖቶች ፤ የኦርቶዶክስ እና እስልምና ጋር በነጋ በጠባ የሚላተም ሥርዓት መካር አጥቶ ወይም ምክር ባይሰማ እንጂ ምን ገጥሞት ነው ይባላል።

ትላንት በአንዋር መስጊድና በተለያዩ አካባቢዎች በጸጥታ አካላትና በእስልምና እምነት ተከታዬች መካከል የተከሰተው ግጭትና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የጸጥታ አካላት ሞትን ጨምሮ ያደረሱት ጉዳት ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ መውደቁን ማሳያ ነው።

ከዚህ በፊት እንዳልኩት የዶ/ር አብየይ አስተዳደር አገሪቱ እንደ ሀገር፣ ሕዝቡም እንደ አንድ አገር ሕዝብ ጸንተው የቆዩባቸውን ምሰሶዎች እያናጋና እያፈራረሰ ይመስላል። ብልጽግና አንድ ቤት አድሳለው ብሎ የቤቱን ምሰሶ እየቦረቦረ በላዩ ላይ ቤቱን እንደሚንድ ቂል ወይም እውቀትና ብልሃት የጎደለው ወይም አእምሮው የታወከ ሰው አይነት ባህሪ ነው የሚታይበት።

የአገዛዝ ሥርዓቱ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለውን ብልሹ ግንኙነት፣ የተጋባውን መጥፎ እልህና ተቋማቱን የማጥቃት ሥራ ቶሎ ካላቆመና ባህሪውን ካላረቀ፤ እንዲሁም አስፈሪ የሚመስሉትን አደጋዎች ቶሎ መቀልበስ ካልቻለ ቤቱ ይናዳል። ያኔ ተያይዘን መዳረሻችን አይታወቅም።

ትላንት በጸጥታ አካላት ሕይወታቸው ያለፈ ሙስሊም ወንድሞቻችንን ነፍስ ይማር! ገዳዬች ለፍርድ ይቅረቡ!

መልካም ሰንበት

LEAVE A REPLY