“ አሳዳጅ በደጅ “ || በእውቀቱ ስዩም

“ አሳዳጅ በደጅ “ || በእውቀቱ ስዩም

የጎጃሙ ገዢ ደጃዝማች ብሩ ደፋርና ሀይለኛ ተዋጊ ነበሩ፤ ተድላ ጉዋሉ የተባለ የስልጣን ተፎካካሪ ነበራቸው ፤ ከለታት አንድ ቀን፤ ተድላ ለደህንነቱ ስለ ሰጋ አባይን ተሻግሮ በሌሎች ገዥዎች ክንድ ስር ለመጠለል አሰበ፤ጥቂት ቦታዎች ያልተሳካ ጥረት ካደረገ በሁዋላ መጨረሻ ላይ ነገዎ ገመዳ የተባለ የጃርሶ(ሰላሌ) ጌታ ጥገኝነት ሊሰጠው ተስማማ፤

ደጃች ብሩ ይህንን እንደ ሰማ በንዴት ጤሰ! “ ጠላቴን ሸሽገህ ይዘሀልና መጣሁልህ “ ብሎ ለነገዎ ማስጠንቀቂያ ላከበት! ነገዎ ገመዳ ማስፈራርያው እንደደረሰው፥ ሰራዊቱን ከየቦታው ባዋጅ ጠርቶ ሰላሌ ሜዳ ላይ ጉግስ ጨዋታ አካሄደ፤ አላማው የፈረሰኞቹን ብዛት እና ንቃት ለጠላቶቹ ለማሳየት ነበር፤ በዛሬው አነጋገር ወታደራዊ ሰልፍ ማካሄዱ ነው፤ ይህንን የተመለከቱ የብሩ ሰላዮች ጉዳዩን ለጌታቸው አመለከቱ፤

ብሩ ግን ከውሳኔው ንቅንቅ አላለም፤ ወደ ሰላሌ ሄዶ የነገዎ ገመዳን ፈረሶች “ ቂጥለቂጥ እንደሚያማታ” ዛተ፤

መካሪ መኮንንኖች ግን እንዲህ አሉት’
“ ግዴለም ይቅርብን! አሳዳጅ በደጅ አንሁን! “

ዋናዋ ነጥብ “ አሳዳጅ በደጅ አንሁን “ የምትለው ምክር ናት! በሰፈራቸው፥ በሜዳቸው ብንገጥማቸው ያሸንፉናል ማለት ነው፤ (ናፖሊዮን ቦናፖርት እንዲህ የተባ መካሪ የነበረው ቢኖው ሩስያ ገብቶ አይዋረድም ነበር)

ደጃች ብሩ የመኳንንቱን ምክር ተቀብሎ ዘመቻውን አጠፈው፤

ፍቅር እስከመቃብር “ በተባለው የሀዲስ አለማየሁ ዝነኛ ልቦለድ ውስጥ ካሉት ዋና ታሪኮች አንዱ የባላገሮች አድማ ነው፤

ፊታውራሪ መሸሻ የተባሉት ጌታ የአመት በአል መዋያ የሚል አዲስ ግብር በባላገሮች ላይ ጣሉባቸው፤ ባላገሮች እምቢ አንከፍልም አሉ፤ ፊታውራሪ ጉልበታቸውን ተማምነው የሚንቁትን ያመጸ ባላገር በዘመቻ ለመቅጣት ቆረጡ፤

መካሮች ተሰበሰቡ፤ የድሮ መካር እንደ ዛሬ “ በለው ! በለው ! “ አይልም፤ ጌታው ፈረስ ከሆነ መካሩ ልጉዋም ይሆናል፤ መካሮች ተናገሩ፤

“ባላገር ሕይወቱንም ጥይቱንም ቆጥቦ ነው እሚዋጋ ፥ ጠላቱ እሱን በመፈለግና በራብና በጥም እስኪደክም ፊትለፊት ተሰልፎ አይገጥምም! ባገሩ እህል ውሃው የሱ ስለሆነ ዱር ገደሉ ተራራው ሸንተረሩ፥ ሁሉም የሱ ስለሆነ ፥ እህል ውሀውን ሸሽጎ፥ እሱ በዱር ገደሉ ተሸሽጎ ብዙ ሰው ሳይሞትበት ፥ ብዙ ጥይት እንኩዋ ሳይጠፋበት፥ ድል ያደርጋል! ያደመ ባላገርን አሸንፋለሁ ብሎ ማሰብ ውቅያኖስን ጠልቄ እጨርሳለሁ እንደማለት ነው “

ፊታውራሪ መሸሻ እንደ ደጃች ብሩ ምክር የሚሰሙ አልነበሩም፤ አሻፈረኝ ብለው ጦራቸውን አስከትለው ወደ አደሙት ባላገሮች ዘመቱ! ባላገሮች አበጀ በለው በተባለ ሽፍታ መሪነት የሚደንቅ ነገር አደረጉ፤ ፊታውራሪ መሸሻ ወደ ሰፈራቸው ዘው ብለው እንዲገቡ በሩን ከከፈቱላቸው በሁዋላ አዘናግተው ፥ ከብበው ፥ ከምክትል ሚስታቸው ጋር በተኙበት ማረኳቸው፤

የምንኖረው በቅራኔዎች በተሞላ አለም ውስጥ ነው፤ ከቅራኔዎች እሚገላግለን ምናልባት ሞት ሳይሆን አይቀርም፤ ፖለቲካ ማለት ቅራኔዎችን ከናካቴው ማስቀረት ሳይሆን ቅራኔዎችን ለከፋ ጉዳት እንዳይዳርጉ አድርጎ ማርገብ ነው፤ የሆነ አካባቢ ማህበረስብ ሲያምጽ የአመጽ ምንጭ የሆኑትን ሮሮዎች እህ ብሎ መስማት፤ ችግሮችን ማዳመጥ እና ለመፍታት መፍቀድ የመንግስት ዋና ስራ መሆን አለበት ፤ ለገበሬ ማዳበርያ በጊዜው ማቅረብ፤ ህዝቡ አስተዳዳሪዎቹን ራሱ እንዲመርጥና እንዲሽር መፍቀድ፥ በሰላም ተዘዋውሮ እንዲኖር ፥ እንዲሰራና የቤት ንብረቱ ባለቤት እንዲሆን ማገዝ፤ ወዘተረፈ…

በተረፈ በገዛ መንደሩ ላይ ወታደር አሰማርቶ ብሶቱን ለማፈን መሞከር ከታሪክም ከስነጽሁም አለመማር ነው፤ ቅራኔዎችን ማራገብ ትተን ቅራኔዎችን ማርገብ ይልመድብን!

LEAVE A REPLY