ለ50 አመታት የቀጠለው እልቂት ይቁም! || ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ

ለ50 አመታት የቀጠለው እልቂት ይቁም! || ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ

በአመታት ውስጥሚሊዬን  ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል”
ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት ፕሬዘዳንት

በኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየታየ ያለው የእርስበእርስ እልቂትና  የሰላም እጦትና መፈናቀል እና
፤ በገዛ ወገኖቻችን የሚፈጸመውን፤ የወገኖቻችንን እልቂት  በአስቸካይ እንዲቆም የኢትዮጵያ የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ኃይለስላሴ በሰጡት መግለጫ አሳሰቡ።

ለ50አመታት የቀጠለው እልቂት ይቁም በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት  በአወጣው መግለጫ “
በቅርቡ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በመራዊ ከተማ፤ ህጻናትንና አዛውንትን ጨምሮ፤ በኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈጸመውን የ102 ንጹሃን ጭፍጨፋ ተገንዝበናል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የተፈጸመ አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ግፍ ነው፡፡ ስለሆነም እንደዚህ ያለውን ድርጊት የምንችልበት ልብ ከአሁን በኋላ አይኖረንም፡፡ በመራዊ የተገደሉት ሰዎች ወንጀል፤ አማራነታቸው፤ የክርስቲያንና የእስላም ሃይማኖቶች ተከታዮች መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ገዳዮቹ ደግሞ ሆን ተብሎ በብዛት ከሌላ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ወታደሮች ናቸው፡፡

በአንድ አመት ውስጥ፤ ቅዠት እንጅ እውነት የማይመስልና የሚዘገንን እንደዚሁም አእምሮ የሚረብሽ ተከታታይ ጭፍጨፋ ስንሰማና ስናይ ቆይተናል፡፡ ቁጥር የሌላቸው ወገኖቻችንም ከቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ በመውደቅ፤ የሰውና የህግ ያለህ በማለት ይገኛሉ፡፡ ከሁለት አመታት በፊት ደግሞ፤ በብሄረሰቦች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች፤ ቁጥር የለሽ የሆኑ ሰዎች በጠባብ ብሄረሰብ መሪዎችና በመንግስት ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ፤ ወደ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያኖች እንደተገደሉ ይገመታል፡፡ ያለው የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት መግለጫ  ሲቀጥል

“መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም፤ በጥቂት የጦር መኮንኖች የተመራው መንፈንቅለ መንግስት፤ የነበረንን ሰላም አናግቶ፤ የግርማዊ ቀዳሚዊ ኃይለሥላሴ መንግስትንም ጥሎና እሳቸውንም ከአንድ አመት በኋላ ገድሎ ከዚያም 60ዎቹን የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣኖች በከርቸሌ እስርቤት ውስጥ እንደጨፈጨፈ አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዘውድ አባላትም በዚያን ጊዜ ተገድለዋል፤ በእስርቤትም ለረዥም ጊዜ ታስረዋል፡፡ ይህም ክስተት፤ በሶቭየት ህብረት የተደገፈውንና በሀገሪቱ ውስጥ ቀይ ሽብር ተብሎ የተጠራውን፤ እስካሁንም ያልቆመውን የጭፍጨፋ ባህል አስከትሏል፡፡

ባለፉት 50 አመታት፤ አብዮተኞች የከፋፍሎ መግዛት መርህ ይዘው፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ለመቀማትና ለማጥፋት ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም፤ በእነዚህ አመታት ውስጥ፤ መሬታችንን፤ ንብረታችንን፤ በህግ ፊት ያለንን መብትና ተስፋችንን ተቀምተናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን፤ የእኛ ያልሆነ ማንንት ሊሰጡን የሚጥሩትን አንቀበልም፡፡ እኛ፤ የአምላክ ቡራኬ ያለን፤ ነጻ ህዝብ የሆንና በክልል አጥር መለያየት የማንፈልግ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡”

የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት በአወጣው በዚሁ መግለጫ “አሁን ያለንበት ወቅት፤ ለ50 አመታት ያህል በተለያዩ የአምባገነን መሪዎች ከተጫነብን የሽብር ዘመን ለመላቀቅ የምናደርገው ትግል እየተፋፋመ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍለግዛቶች ሁሉ የፍትህ ትግሉ ተቀጣጥሏል፡፡ ሆኖም ግን፤ ፍትህና ተቀባይነት ያለው የህግ አስተዳር ካልመሰረትን፤ የምናደርገው ትግል ሁሉ ዋጋቢስ ይሆናል፡፡ ትግላችን ፍትህን ለማምጣት እንጅ፤ አንድን ግጭት በሌላ ግጭት የመቀየር አላማ መሆን የለበትም፡፡” ሲል ያሳሰበው የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት መግለጫ
በእነዚህ 50 አመታት ውስጥ፤ የኢትዮጵያ ዘውድ ህልውናውን አላጣም፡፡

አሁንም እንደበፊቱ፤ ሰላም፤ ፍትህና ፍቅር በኢትዮጵያዊያኖች መካከል እንዲኖርና እንዲዳብር ይጥራል፡፡ ስለሆነም፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶችና ክፍለግዛቶች ውስጥ የተነሱትን የፋኖን ታጣቂ ቡድኖች የምናሳስበው፤ አላማቸው ፍትህንና ተጠያቂነትን ለማስከበርና በህዝቦቻችን መካከል ፍቅርና ብልጽግና እንዲመጣ ማድረግ እንጂ የበቀል ትግል መሆን እንደሌለበት ነው፡፡

በግርማዊ ቀዳሚዊ ኃይለሥላሴ ትእዛዝ መሰረት በመረቀቅ ላይ የነበረው የ1966ቱ ህገመንግስት፤ በስራ ላይ እንዲውል ማድረግ፤ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ይህም ህገመንግስት፤ የተረጋጋ አስተዳደርና መንግስት እንዲፈጠር እንዲሁም ለመራዊ ህዝብ ጭፍጨፋ፤ ለ60ዎቹ ባለስልጣኖች ግድያና በሚሊዮን

ለሚቆጠሩ ሀይዎታቸውን ላጡ፤ ለተሰደዱ፤ ለተራቡና ለተጠሙ ኢትዮጵያውያኖች የፍትህ ጎህ የሚቀድ መሆን አለበት፡፡

ይህን የ50 አመታት እንባ፤ የተቃጠለ ጊዜና የእልቂት ዘመን፤ ወደፊትም የሚቀጥል ሳይሆን ያለፈ ትዝታ እናድርገው፡፡ ልክ ጣልያንን ሁለት ጊዜ ሙሉ ያሸነፍንባቸውን ቀናት እንደምናስታውስና እንደምናከበር ሁሉ፤ አሁን የምናገኘውን ድልም፤ ለዘላለም እናከብረዋለን፡፡ በታላቆች ንጉሰነገስቶቻችን፤ በግርማዊ ዳግማዊ ምኒልክና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተጀመሩት የኢኮኖሚና የማህበራዊ አውደ ሂደቶች መማርና እነሱም ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ ታሪክ በሚረሳቸው አምባገነን መሪዎች ወደኋላ የቀረችውን ኢትዮጵያን እንደ አዲስ እንገነባለን፡፡

የአሁኑ አላማችን፤ በወቅቱ የሚካሄድውን ጦርነትና ግጭት፤ ብዙ የደም መፋሰስ ሳያስከትል አስቁመንና ቂም በቀልነትን አስወግደን፤ ሁሉን አቀፍ ፍትህ እንዲመጣ መጣር ነው፡፡ ይህም ጥረታችን፤ ዲሞክራሲያዊ አሰራር እንዲኖርና የማያቋርጥ ብልጽግናና ክብር በሀገራችን እንዲሰፍን ይረዳናል፡፡”ሲል ለሁሉም ኢትዬጵያውያን ወገኖች ጥሪውን አቅርቦል፡፡

LEAVE A REPLY