ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ 20 ቦይንግ 777 ኤክስ 9 የተሰኙ ግዙፍ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ዛሬ የካቲት 26ቀን2016 በአዲስ አበባ የውል ስምምነት አደረገ።
በ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳና የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አርቭን ሆሴ ማሲንጋና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች በተገኙበት በተካሄደ ስነ ስርአት የስምምነት ሰነዱ የተፈረመው ::
በፊርማ ስነስርአቱ ላይ ንግግር ይደረጉትየኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ይህ አውሮፕላን በግዙፍነቱና በአይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው።
ትዕዛዝ ከተፈፀመባቸው 20 የቦይንግ 777 ኤክስ 9 አውሮፕላኖች መካከል ስምንቱን እ.አ.አ እስከ 2030 አየር መንገዱ የሚረከብ መሆኑን በዚህም መሰረት 3ቱ በ2027 3ቱ በ2029 እንዲሁም 2ቱ በ 2030 የሚረከቡ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
ይህ ግዙፍ አውሮፕላን እያንዳንዱ 440 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን 15 የቢዝነስ ክፍል መቀመጫ እንዳለውም ታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ህዳር ወር 2016 ዓ.ም በቅርቡ ከቦይንግና ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያዎች በድምሩ 84 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ለመግዛት ሥምምነት ማድረጉ ይታወሳል።
በተጨማሪም በጥናት ላይ የተመሰረተ ተመሳሳይ የአውሮፕላን ትዕዛዞችን ለማድረግ መታቀዱንም ገልጾ ነበር።
ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገትን በመከተል ዓለም ላይ ካሉ 20 ምርጥ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።