ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቱርክና ሶማሊያ ነዳጅ ዘይትና ጋዝ የመፈለግና የማውጣት ትብብር ስምምነት ላይ ደረሱ ። ቱርክ እንዳለችው ሁለቱ ሀገራት ትናንት ኢስታንቡል ውስጥ የተስማሙበት ይህ ውል በሶማሊያ ምድርና የባህር ዳርቻ ነዳጅ ዘይት መፈለግ፣ማውጣት፣ ማልማት እና ማምረትን ያካትታል።
የቱርክ የኃይል ሚኒስትር አልፓርስላን ባይራክታር በኃይል ዘርፍ በሚደረጉት በነዚህ ትብብሮች ቱርክ ከአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን የማጠናከር ዓላማ እንዳላት በቀድሞው አጠራሩ በትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል። ቱርክ ህንድ ውቅያኖስና የኤደን ባህረ ሰላጤ በሚያዋስኗት በሶማሊያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ከሚፈልጉ ሀገራት አንዷ ናት።
ቱርክና ሶማሊያ ከዚህ ቀደምም የሶማልያን የባህር ሀብት የሚያስጠብቅ የተባለ የመከላከያ ውል መፈረማቸውን ሶማሊያ አስታውቃ ነበር። በየካቲት መጀመሪያ ላይ በተፈረመው በዚህ ውል ሶማሊያ የውሀ ግዛቷን ከሽብር፣ ከባህር ላይ ወንበዴዎች እና ከውጭ ጣልቃገብነት መጠበቅ እንድትችል ቱርክ ለሶማሊያ የባህር ኃይል ስልጠናና ቁሳቁስ ትሰጣለች።
የሶማሊያ ባለስልጣናት ለአስር ዓመታት ስራ ላይ ይቆያል ያሉት የመከላከያ ውሉ ኢትዮጵያ ራስዋን ከሶማሊያ ከገነጠለችው ከሶማሌላንድ የባህር ወደብ እንዳይኖራት የማገድ ዓላማ ያለው ነው ብለው ነበር።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ በሊዝ የባህር ወደብ እንድታገኝያስችላታል የተባለው የመግባባቢያ ሰነድ 2024 አዲስ አመት የመጀመሪያ ቀን መፈራረማቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ በምትኩ ለሶማሌላንድ እውቅና ለመስጠት ተስማማታለች ሲሉ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት በወቅቱ ተናግረዋል።
ይህ የቱርክዬ እና የሶማሊያ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ የማውጣትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚይስችል ስምምነት ይፋ ሲሆን የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ መንግስታት ደርሰውበት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነዱ ዝርዝርግን እስካሁን ይፋ አልሆነም። en