ህዳሴ ግድብ እስከ ሐምሌ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይደርሳል

ህዳሴ ግድብ እስከ ሐምሌ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይደርሳል

–                  ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ግድቡ ውኃው መያዝ ያለበትን ቁመት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይደርስል። አገራዊ ለውጡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ከነበረበት ውስብስብ የግንባታ ሂደት በማውጣት ለስኬት እንዲበቃ ማድረጉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ከአገራዊ ለውጡ በፊት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበት ወደ መቆም ደርሶ ነበር። በተለይም ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚሰጡት ገንዘብ አቅም በሌለው ተቋራጭ የግንባታው ሂደት እንዲመራ መደረጉና የተሰበሰበው ገንዘብ ሲመዘበር መቆየቱንም ተናግረዋል። 

ይህ ተገቢ ያልሆነ የፕሮጀክት አስተዳደርና ሆን ተብለው የተፈጸሙ ብልሹ አሠራሮች በግንባታው አጠቃላይ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሳቸውንና ይህም አሳዛኝ ክስተት እንደነበር ነው ያነሱት።  

እንዲያም ሆኖ በአገራዊ ለውጡ ማግስት የግድቡን ቀጣይ ሂደት ለመወሰን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተከናወነው ይኸው ሥራ ግድቡን ከገባበት ችግር በማውጣት ረገድ ትልቁ የስኬት መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በፊት ፕሮጀክቱ ለስም የተቀመጠ እንጂ ተጨባጭ ሥራዎች እንዳልነበሩበት የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ ወዲህ ሕዝቡ በየዓመቱ የሚቆጠርና የሚለካ ውጤት ማየቱን ተናግረዋል። 

ለአብነትም ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻላቸውን፤ የአገራዊ ለውጡ ስኬት ማሳያ መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት። 

ግድቡ የኢትዮጵያውያንን ከፍታ የሚያረጋግጥ መሆኑን ያወቁ አካላት ግድቡ ሲጀመር ያላሰሙትን ጩኸት በለውጡ ማግስት ማሰማታቸውን አንስተው፤ ይህም ሲጀመር አይጠናቀቅም የሚለው እምነታቸው በለውጡ አመራር ስለከሸፈ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በርካታ ውጣ-ውረዶችን ያለፈው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሁን ላይ ቁመቱን ከመጨመር አልፎ በተለያዩ ዙሮች የውኃ ሙሌት በማድረግ ግድቡ አሁን ላይ ማንም ወደኋላ ሊቀለብሰው በማይችልበት፤ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ትምህርት በሚሰጥ ደረጃ መገንባቱን ነው ያስረዱት። በለውጡ አመራር ግድቡ ዛሬ ላይ ለስኬት መብቃቱን ገልጸው፤ አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 95 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 

በዚህ ዓመት ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ግድቡ ውኃው መያዝ ያለበትን ቁመት የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አመላክተዋል። en

LEAVE A REPLY