በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የልዑካን ቡድንን ተቀብለዉ አነጋገሩ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የልዑካን ቡድንን ተቀብለዉ አነጋገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና | በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በሰሜን ካሊፎርኒያ እና አካባቢዉ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሚመራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ኅብረት የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸዉ ተቀብለዉ አነጋገሩ።  

   ብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ህብረት ለሚሲዮኑ  የካቲት በ27/06/2016 ዓ.ም የተፃፈ ባለ ስድስት ነጥቦች ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ  አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል። ህብረቱ  ካነሳቸዉ ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ፀሃፊ እና የኒዉዮርክ እና አካባቢዉ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ የብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በሲኖዶሱ ፈቃድ ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ ወደ ኒዉዮርክ ሄደዉ ሲመለሱ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ የመከልከላቸዉ ምክንያት ግልጽ ያለመሆን እና መንግስት ይህን ያደረገበትን ምክንያት እንዲገለጽላቸዉ ጠይቀዋል። ድርጊቱ ቅድስት ቤተክርስቲያኒቷን የማይመጥን፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚጋፋ እንደሆነ በማንሳት በአግባቡ ታይቶና ተጣርቶ አስፈላጊዉ የማስተካከያ እርምጃ በመንግስት በአፋጣኝ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። 

በተጨማሪ ከሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት በኤምባሲ እና በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ዕዉቅና አግኝቶ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ቴሌ ቪዥን የቀጥታ ስርጭት  አገልግሎት ለማስጀመር እንዲቻል፣ በእርዳታ የተላኩ በርካታ የቴክኖሎጂ ዕቃዎች  ያላንዳች በቂ ምክንያት ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ፣  በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ  ገዳም መነኮሳት ላይ በግፍ የተፈፀመዉ አሰቃቂ ግድያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ የድርጊቱ ተጠያቂ ማን እንደ ሆነ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዉ የነበረ ሲሆን  በእነዚህ  እና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ዉይይት ተካሄዷል። 

በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ኅብረት ለኤምባሲያችን የተላከዉ ደብዳቤ ምላሽ ያገኝ ዘንድ  ለኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚልኩ እና ቀጣይ ክትትል እንደሚያደርጉ በማንሳት  በሚስዮን ደረጃ መመለስ ያለባቸዉ ጉዳዮችን ደግሞ በመለየት ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ገልፀውላቸዋል። en

LEAVE A REPLY