ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ከመላው ኢትዮጵያ የሲሲቲቪ ካሜራ በብዛት የተገጠመባት ተወዳዳሪ የሌላት ከተማ መሆንዋ ተዘገበ።
የሀዋሳ ከተማ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዲና መሆንዋን ተከትሎ የከተማው አስተዳደር እና የክልሉ መንግስት በርካታ ሚሊዬን ብር በመመደብ ወደ አንድመቶ የሚጠጉ ካሜራዎችን ገዝቶ በዋና ዋና አውራጎዳናዎች አደባባዬች መትከሉ መዘገቡ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ 590 የግል ተቋማት ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመናበብ የራሳቸው የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ ተደርጓል ሲል የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የከተማው ፖሊስ እነዚህ በብዛታቸው በመላው ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ያልተገኝለት የሴኪዩሪቲ ካሜራ ስራ ላይ በማዋል ስኬታማ ሥራ እየሰራሁ ነው ይበል እንጂ እነዚያ ካሜራዎች የሚያስተላልፉት ምስል የሚከታተሉበት የክትትል ባለሙያና ስቱዲዬ ይኖራቸው ይሆን ብዬ ሁል ጊዜ እጠይቃለሁ ሲሉ አንድ በሀዋሳ ዩንቭርሲቲ መምህር የሆኑ የውጭ ዜጋ ስሜን አትጥቀስ ብለው ለኢትዮጵያ ነገ እስተያየት ሰጥተዋል።
የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አንድ ሹም በከተማዋ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተደጋጋሚ ወንጀል የሚፈጸምባቸው አካባቢዎችን በመለየት 40 የፖሊስ መረጃ መቀበያና ማረፊያ ማዕከላት መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ማዕከላቱ ህብረተሰቡ ከወትሮው በበለጠ ከፖሊስ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡና የጸጥታ ሀይሉ ባደረገው ቅንጅት በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል። en