ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሽብርተኛ ተብሎ በተሰየመዉ የሸኔ ሽብር ቡድን ዉስጥ ከ2015 እና 2016 ዓ.ም ጀምሮ በህግ ቁጥጥር ስር እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ ከቡድኑ አመራሮች ጋር በመገናኘትና አባል በመሆን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠናዎችን በመውሰድ፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ እና ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ዉስጥ የመንግስት አመራሮችን እና የአከባቢዉን ነዋሪዎች ማገት፣ መደብደብ፣ መዝረፍ እና ህብረተሰቡን በማስገደድ የሽብር ድርጊት በመፈፀም በሰዉ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሲያደርጉ ነበር በማለት ዐቃቤ ህግ ክስ መሰረተባቸው።
ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገ መንግስታዊና በህገ መንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።
ፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ተከሳሾቹ በ1996 ዓ .ም የወጣዉን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ)እና አንቀጽ 38 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጣር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 1 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀፅ 4 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።
1ኛ ተከሳሽ ፥ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ አመራሮች እና አሰልጣኞች ከሆኑት ጃል ጨጨብሳ፣ ጃል ዲና፣ ጃል ዋቆ፣ ጃል ሰኚ፣ ጃል ወቢና ጃል ፈልሚ ጋር በመገናኘት በኦሮሚያ ክልል ሙገር ጫካ ዉስጥ ለአንድ ወር ከሦስት ሳምንት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ስልጠናዎችን ከወሰደ በኋላ ሙሉ የጦር መሳሪያ ትጥቅ በመታጠቅ የሽብር ቡድኑ ሸኔ ታጣቂ ቡድን አስተባባሪ በመሆን ከመንግስት ፀጥታ ሀይሎች ጋር በመዋጋት፣ የቀበሌ ሚኒሻዎችን ትጥቅ ማስፈታት ህብረተሰቡን ፣ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮችን፣ የሀይማኖት አባቶችን በማገት፣ በመደብደብ፣ በማስፈራራት ገንዘብ እና ንብረት በመዝረፍ መረጃ እና ሎጂስቲክ በማሰባሰብ የሽብር ቡድኑን በማስተባበር እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽን ቡድኑን እንዲቀላቀል በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ዉስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።
ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከለሊቱ 7፡00 አካባቢ ይኸው አንደኛ ተከሳሽን 2ኛ ተከሳሽ ተቀብሎ በሱሉልታ በሚኖርበት የወላጆቹ መኖሪያ ቤት ከእነሙሉ ትጥቁ በማሳደር 1ኛ ተከሳሽ ታጥቆ የመጣዉን የተለያዩ የጦር ማሳሪያዎች ማለትም 1ኛ- አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ 103 ጥይቶችጋር ፣ 40 የብሬን ጥይቶች፣ 2 ኤፍ1 ቦምቦች እና አንድ ወታደራዊ ትጥቅ በቤቱ ዉስጥ ቆፍሮ የቀበረ እና ጥር 9 ቀን 2016ዓ.ም በፀጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉ በመሆኑ በክሱ ተመላክቷል።
3ኛ ተከሳሽ ደግሞ የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር በመንቀሳቀስ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ .ም ከሌሊቱ 4 ሰዓት ላይ 12 ከሚሆኑት የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎችን መንገድ እየመራ የቀበሌ አመራር ወደ ነበረዉ የግል ተበዳይ የሆነው መኖሪያ ቤትን ሰብሮ በመግባት በክላሽ ሰደፍ በመደብደብ የአካል ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ከቤት ዉስጥ 47 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ እና አንድ የቱርክ ሽጉጥ በመዝረፍ፣ የቤት ንብረቱን በመሰባበር፣ እንዲሁም ግለሰቡን በማገት እየደበደቡ ወደ ጫካ ሲወስዱ መንገድ ላይ ወድቀዉ ሞተዋል ብለዉ ህይወታቸው እንዲያልፉ ያደረገ በመሆኑ ዐቃቤ ህግን ጠቅሶ ክሱ አስፍሯል።
በተመሳሳይ ከለሊቱ 4፡30 ስማቸዉ ያልተለየ እና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 12 የሚሆኑ የሸኔ ታጣቂዎችን መንገድ እየመራ የቀበሌ ሚሊሻ የነበረ አንድ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ሰብሮ በመግባት በክላሽ ሰደፍ በመደብድብ ባለቤቱ ስትጮህ በጥፊ በመምታት ግለሰቡን በማገት ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር እንዲታገት አድርገዉ ታጣቂዎቹ የሁለት ቀን የእግር ጉዞ በማስኬድ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅራቢያ በረሃማ ጫካ ዉስጥ ካደረሱ በኋላ “ከመንግስት ጋር ስለምትስራ 400 ሺህ ብር መክፈል አለብህ የማትከፍል ከሆነ ባለቤትህን እንገድላለን” በማለት በማስፈራራት 60 ሺህ ብር ከፍሎ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ከእገታ የተለቀቀ በመሆኑ በክሱ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ጥር 17 ቀን 2015ዓ.ም ከለሊቱ 3፡40 አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ከሌሎች ማንነታቸዉ ያልተለዩ 3 የሽብር ቡድኑ ሸኔ ታጠቂዎችን እያመራ ወደ አንድ ግለሰብ ቤት በመዉሰድ በማገት ከሌሎች 5 ታጋቾች ጋር ወደ ጫካ እንዲወሰድ ካደረገ በኋላ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅራቢያ በረሃማ ጫካ ዉስጥ ቡቢሳ የሚባል ቦታ ካደረሱ በኋላ ‘‘አንተ ነህ ከመንግስት ጋር እያሰራህ እኛን የምታስይዝ’’ በማለት ሲደበድቡት እና ሲያሰቃዩ ከቆዩ በኋላ አንድ ሽጉጥ ቀምተዉ 70 ሺህ ብር ከፍሎ ከእገታ የተለቀቀ በመሆኑ እና ከተለቀቀ በኋላም የፀጥታ ስራ እንዳይሰራ በተደጋጋሚ ዛቻ እና ማስፈራራት የፈፀመበት በመሆኑ በክሱ ተመላክቷል።
4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሱሉልታ ከተማ መቀመጫዋን በማድረግ ታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ አመራር ከሆነዉ ከጃል ሞርከታ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከሁለት ግለሰቦች 120 ሺህ ብር ከተቀበለች በኋላ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ጫማ (ከስክስ) መግዣ በማለት ለ3ኛ ተከሳሽ ገዝቶ እንዲልክ በመስጠት ለሽብር ቡድኑ አመራር ለሆነዉ ለጃል ሞርካታ ጫማዉ እንዲደርሰዉ ማድረጓን እና በቀሪዉ 100 ሺህ ብር ደግሞ 100ኪሎ ግራም ጤፍ፣ አራት የሞባይል ቀፎዎች፣ የአንገት ሃብሎችን ጭምር በመግዛት ለሽብር ቡድኑ እንዲደርስ ማድረግ እና 10 ፍሬ የፌዴራል ፖሊስ ሙሉ ደንብ ልብስ ተቀብላ ለሽብር ቡድኑ ለማስተላለፍ በመኖሪያ ቤት ዉስጥ አስቀምጣ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በፀጥታ ሀይሎች የተያዘች በመሆኑ በክሱ ተመላክቷል።
በተጨማሪም በ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ላይ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላላፍ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሱሉልታ ክፍለ ከተማ አባገዳ ወረዳ በ2ኛ ተከሳሽ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ዉስጥ ብዛት ያለዉ የጦር መሳሪያዎች መሬት ውስጥ ቀብረዉ በፀጥታ ሀይሎች የተያዙ መሆኑ ተጠቅሶ የጦር መሳሪያ መደበቅ ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ዋስትና ላይ ክርክር ለማከናወን ለመጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል። (en ኢትዮጵያ ነገ)