ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አማራ ክልል ውስጥ ሽንፋ እና መተማ አካባቢዎች በቅሪተ አካል ግኝት የተለዬ የተባለ ግኝት መገኘቱ ተገልጿል። ግኝቱ ጥንታዊ የሰው ልጅ አኗኗርን እና እንዴት ከአፍሪካ ወደ ሌሎች ዓለማት ይሻገር እንደነበር የሚያሳይ ስለመኾኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ትላንት መጋቢት11/2016 በሰጠው መግለጫ እንዳመላከተው ጥንታዊ ሰው እንዴት ከአፍሪካ ወደ ሌሎች አሕጉራት ተሻገረ ለሚለው ጥያቄ ምርምር ለማድረግ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሽንፋ እና መተማ ረባዳ ቦታዎች አካባቢ ለ22 ዓመታት ያህል ምርምር ሲደረግ ቆይቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓልዮአንትሮፖሎጂ እና ፓልዮኢንቫይሮመንት ተመራማሪ የኾኑት ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ እና በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የኾኑት ዶክተር ጆን ካፕልማን ( የሚመራ የጥናት ቡድን ከባለስልጣኑ ባገኘው ፈቃድ ነው ምርምሩን ሲያካሂድ የቆየው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር የጥናት ቡድኑ ብዛት ያላቸው የመካከለኛ ዘመን የድንጋይ መሳሪያዎችን እና የእንስሳት ቅሪተ አካላትን አስሶ በማግኘት የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። መካነ ቅርሱ የሚገኝበትን ሥፍራ ሥነ ምኅዳር በማጥናት በአይነቱ የመጀመሪያ የኾነ መረጃ መገኘቱንም ገልጸዋል። የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሌንሳ መኮንን እንደ ሀገር ምድረ ቀደምት የሚያደርጉን ብዙ ምርምሮች እና ቅርሶች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።
የጥናት ቡድኑ ተባባሪ መሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ ግኝቱ ከሌሎች ግኝቶች የተለዬ ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች ወንዝን ተከትለው ይኖሩ እንደነበር አዲስ ዕይታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የጥናቱ ውጤት ዋና ይዘት ጥንታዊ ሰዎች የድንጋይ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአካባቢው ይገኙ የነበሩ እንስሳትን በማደን ይመገቡ እንደነበር የሚያሳይ ነው ብለዋል። በኩሬዎች ይኖሩ የነበሩ እንደ ዓሳ እና የመሳሰሉትን የውኃ ውስጥ እንስሳት በመመገብ በረሃማ የአየር ንብረቱን ተቋቁመው ይኖሩ እንደነበረ የሚጠቁም ጥናት እንደኾነም ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጥናቱ ጥንታዊ ሰው ሞቃታማ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ የመኖርና የመላመድ ባህርይ እንዳዳበረ እና በአካባቢው የነበሩ ዓሳ እና መሰል ምግቦች ሲያልቁበት ከኩሬ ወደ ኩሬ በመጓዝ ወንዝ ተከትሎ በረሃማ ቦታዎችን ሲሻገር እንደነበር የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል።
ሌላው ትልቁ ግኝት በአካባቢው ባሉት ንብርብር አለቶች ውስጥ የተገኘው የእሳተ ገሞራ አመድ ነው። ይህ ግኝት ከሽንፋ እና መተማ 7 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በኢንዶኔዥያ ሰማትራ ከ74 ሺህ ዓመታት በፊት የፈነዳው የእሳተ ገመራ አመድ መኾኑ በጥናቱ ስለመረጋገጡ ተነግሯል።
የጥናቱ ውጤት ጥንታዊ ሰው ከአፍሪካ ወደ ሌላ አሕጉራት ለመሻገር በፊት ይታሰብ እንደነበረው ለምለምና በዛፍ የተሸፈነ መሬትን ተከትሎ ሳይኾን ደረቅ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ እንደነበር ያመላከተ ነው። ይህም አዲስ የምርምር ዕይታ እና አቅጣጫ የሚያመላክት መኾኑን የጥናት ቡድኑ ተባባሪ መሪ ተናግረዋል ።
በምርምሩ ከሀገር ውስጥ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከ30 በላይ ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል። የምርምር ግኝቶቹም የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው ይፋ የተደረጉት። (EN – ኢትዮጵያ ነገ)