የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሀላፊ የቤተ ክርስቲያን ፈተናን በተመለከተ መግለጫ ሰጡ

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሀላፊ የቤተ ክርስቲያን ፈተናን በተመለከተ መግለጫ ሰጡ

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም 

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ (ቀሲስ) በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተና እና ችግር በተመለከተ የሰጡት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ስለወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ።

እግዚኦ ቦኡ አሕዛብ ውስተ ርስትከ ወአርኰሱ ጽርሐ መቅደስከ ወረሰይዋ ለኢየሩሳሌም ከመ ልገተ ዓቃቤ ቀምሕ ፤ አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጓት መዝ 78:1

ጥንታዊት ፣ ታሪካዊት ፤ ሐዋርያዊት ፣ ዓለም አቀፋዊት እና ኢትዮጵያዊት ፊተኛዪቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በታሪክ ፣ በትምህርት ፣ በኪነ ሕንጻ እና በመሳሰሉት ሁለተናዊ ቁልፍ ጉዳዮች ያበረከተችው በጎ አስተዋጽኦ ማንም ሊክደው የማይችል ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው።

ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ታላቋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገር ክብር ለሕዝቦቿ አንድነት የዋለችው ውለታ ተዘንግቶ ክብሯን በሚነካና መብቷን በሚጋፋ ሁኔታ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ አበው ያለ ስሟ ስም በመስጠት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ፣ በአገልጋይ ካህናት ላይ እና በምእመናን ልጆቿ ላይ በርካታ አሳዛኝ እና ልበ ሰባሪ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ፣ አሁንም ባላሰለሰ ሁኔታ እየተፈጸሙ ይገኛሉ።

በዚህም መሠረት በሀገረ ስብከታችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቅጥራቸው ተደፍሮ ፈርሰዋል ንዋያተ ቅድሳቶቻቸው ተቃጥለዋል ካህናት አገልጋዮቿ ተገለዋል ምእመናን ልጆቿ ሞተዋል ከሞቀ ቀያቸው ከደመቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ለከፋ የሕይወት እንግልት ተዳርገዋል።

ችግሩ ከነገ ዛሬ ይቀላል በማለት በትዕግሥት ለማለፍ በአባቶቻችን መንገድ እና ጥበብ ለማለፍ ብንሞክርም ችግሩ ግን ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ በጣም አዝነናል ልባችንም በእጅጉ ተሰብሯል።

አሁን እንኳን በዚህ ታላቅ ጾም ተረጋግተን ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር በፍጹም ንስሐ መልሰን ስለሀገራችን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እና ስለሕዝባችን ሰላም በምናለቅስበት ሰዓት ሁልጊዜ የመከራ ገፈት ቀማሽ በሆነው የይፋት ቀጠና ከዚህ በፊት የተቃጠሉብንን አብያተ ክርስቲያናት መልሰን ሠርተን ለማክበር ጫፍ ስንደርስ እያፈረሱብን በሀዘን ላይ ሀዘን እየተጨመረብን ይገኛል።

አሁንም በዚህ ወቅት በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ቤተ ክህነት የካሬ ቆሬ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ ወድሟል የሞላሌ ቅዱስ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተጎድቷል።

በተመሳሳይ በቀወት ወረዳ ቤተ ክህነት የኩሪብሪ ቅዱስ ሚካኤል እና የዋጮ ቅዱስ በዓለ ወልድ አብያተ ክርስቲያናት መጎዳታቸውን እና የየለን ቅድስት ማርያም ንዋያተ ቅድሳት መዘረፉ ሀዘናችንን እጽፍ ድርብ አድርጎታል።

ስለዚህ፦

1.ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ቤት የአንድነት ተምሳሌት የሀገር ባለውለታ ያለ ቋንቋ ፣ ያለዘር እና ያለከለር ልዩነት ለሁሉም በእኩልነት መንፈሳዊ አገልግሎቷን ተደራሽ አድራጊ መሆኗ ታውቆ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደረገውን ግፍ እና አስነዋሪ ነገር ሁሉ በፅኑዕ እንቃወማለን የሚመለከተው አካልም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጸውን ድፍረት የተሞላበት በደል እና ነውር ያስቆምልን ዘንድ በአጽንኦንት እንጠይቃለን።

2.የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ የሚገባው አካል የምእመናን ልጆቻችንን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ሰላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ወደ ቤት ቀያቸው እንዲመለሱ አስፈላጊው ሁሉ ይደረግልን ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናሳስባለን።

3.ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በይፋት ቀጠና እና በምንጃር ወረዳ ቤተ ክህነት ከአውራ ጎዳና አካባቢ ከቤታቸው እና ከቀያቸው ተፈናቅለው ላሉ ወገናቻችን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን በሙሉ የድጋፍ እጃችሁን ትዘረጉልን ዘንድ በጸሎታችሁም ታስቡን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን። የሚል መግለጫ እውጥቶል (en ኢትዬጵያ ነገ)

LEAVE A REPLY