ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ያጋጠመውን የሳይበር ችግር ተከትሎ ጤናማ ያልሆኑ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑ ተገለፀ።
በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች መረጃ ላይ ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራም አገልግሎቱ ገልጿል።
አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ሲሆን የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ያንቀሳቀሱና ወጪ ያደረጉ ግለሰቦች ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎም በርካቶች እየመለሱ መሆኑን ጠቁሟል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊና የራስ አስመስሎ የማቅረብና የመጠቀም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኃላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረትም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ/ንብረት መውረስ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ መደንገጉን በመግለጫው አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ችግር ማጋጠም ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ክፍተት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያደረጉና በእስከ አሁኑ ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችን መረጃ በመከታተል ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም ያረጋግጧል ብሏል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት። (EN – ኢትዮጵያ ነገ)