መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶችንና ምእመናንን አሰቃቂ ግድያ በማስቆም ከደሙ ነጻ መሆኑን በአስቸኳይ ሊያረጋግጥ ይገባል!
አገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች መገኛ ናት። እናት ፓርቲ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከረው ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶቻችን የአገራችን መሠረቶች ናቸው። መንግሥት እነዚህ መሠረቶቻችን የማይታለፉ አይነኬ ቀይ መስመሮች መሆናቸውን በአግባቡ ሊገነዘብ ይገባል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምዕመናን ባለፋት ሶስት አስርት ዓመታት እጅግ በጣም አሰቃቂ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በቤተክርስቲያኗ እና ምእመናኗ ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ግፍና አሰቃቂ ግድያዎች ክፉኛ ተጠናክረው ቀጥለዋል። መንግሥት እስካሁን እየተፈጸሙ የሚገኙትን አሰቃቂ ግድያዎች አስተውሎ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አልቻለም። ይልቁንም የቤተክርስቲያኒቱና የምዕመናኗ መከራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ከምሽቱ ፫:፳ ጀምሮ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መርጌታ፣ ሁለት ልጆቻቸው እና ባለቤታቸውን ጨምሮ ከሁለት ወራት በፊት ሥርዓተ ጋብቻቸውን የፈጸሙ ሙሽሮች (አንድ ዲያቆን ከባለቤቱ እና ታላቅ እህቱ ጋር) በአጠቃላይ ፯ ንጹሐን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ካህናትና ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ በታጣቂዎች መገደላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም ከደቡብ ክልል አካባቢ መጥተው በከተማው በቀን ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ፬ ንጹሐን ዜጎችም በታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውንና ሌሎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ፯ ሰዎችም በዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ለመረዳት ችለናል።
ከዚህ ማብቂያ ካጣው አሰቃቂ ግድያ ጋር በተያያዘ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶችና ምእመናንን አሰቃቂ ግድያ በማስቆምና መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ከእነዚህ ንጹሐን ደም ነጻ መሆኑን በአስቸኳይ ሊያረጋግጥ ይገባል ብለን እናምናለን።
በመጨረሻም በታጣቂ ኃይሎች ለተገደሉት ንጹሐን ዜጎቻችን እረፍተ ነፍስን እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ፈጣሪ እንዲሰጥልን እንመኛለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ