በአዲስ አበባ ሁለት የፌደራል ፖሊሶች ተገደሉ
በዛሬ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በስራ ላይ ባሉ የፌደራል ፖሊሶች መሐል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ፡፡
ፌደራል ፖሊስ የጥበቃ አገልግሎት ከሚሰጣቸው መንግስታዊ ተቋማት መሐል አንዱ በሆነው የፌደራል ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ግቢ ውስጥ ነው ችግሩ የተከሰተው፡፡
ኤጀንሲውን ከሚጠብቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል አንዱ ለተመሳሳይ ስራ ወደ ሌላ ተቋም መቀየሩ፣ ለግጭቱና ለግድያው መንስኤ መሆኑን በስፍራው ከነበሩ ሌሎች የጥበቃ አባላት ሰምተናል፡፡
በሓላፊው የተነገረውን የጥበቃ ቅየራ ቦታ ያልተቀበለው የፌደራል ፖሊስ፤ ከአለቃው ጋር በጉዳዩ ላይ ያደረገው ውይይት ወደ ከፍተኛ አለመግባባት ደርሶ ፖሊሱ ሓላፊውንና በስራ ላይ የነበረን አንድ የፌደራል ፖሊስ በያዘው መሳሪያ ገድሏል፡፡
ሕግን በማስከበር፣ የሕዝብን፣ የሃገርን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ላይ የተሰማሩ የሙያ ባልደረቦቹን በስሜታዊነት የገደለውየ ፌደራል ፖሊስ አባል በአሁኑ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የኢትዮጵያ እና ሱዳን ደህንነቶች በጋራ ሊሰሩነው
ከአልበሽር ውድቀት በኋላ የበለጠ ወዳጅነታቸው እየጠነከረ የመጣው ኢትዮጵያ እና ሱዳን በደህንነት ተቋማቸው አማካይነት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተነግሯል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የሱዳኑ ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል አቡበከር ዳምብላም አብሮ የመስራት ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡
በድንበር ወሰን አካባቢ የሚፈጠሩ የተደራጁ ወንጀሎችን በመከላከል፤ ከኹለቱም ሃገራት የተውጣጣ የፀጥታና የደህንነት ሓላፊዎች ያሉበት ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራውን እንደጀመረም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን ሰላማዊ ሽግግር እውን እንዲሆን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ሱዳን የምስጋና ፕሮግራም አዘጋጅታለች፡፡
ኢትዮጵያና አፍሪካ ሕብረት ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ላበረከቱት አስተዋፅኦ እና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና ምስጋና ከመቅረቡ ባሻገር ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ለጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የሱዳን ልዩ ልዑክ አምባሳደር መሀሙድ ድሪር፣ በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ መሀመድ ሀሳን ላባት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ሲጓዙ የሞቱት 16 ኢትዮጵያዊያን በትግራይ የኢሮብ ተወላጆች መሆናቸው ታውቀ
ተደጋጋሚ የባህር ላይ አደጋ የሚከሰትበት፣ በሊቢያ ወደጣሊያን የሚደረገው አሰቃቂው ስደት ዛሬም ለኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ዜናን ይዞ መጥቷል፡፡
“ያልፍልኛል” በሚል የባህር ላይ ስደትን መርጠው ወደ ሊቢያ ከተጓዙ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሀል አስራ ስደስቱ ሕይወታቸውን ለግዙፉ ውቅያኖስ ገብረዋል፡፡ አደጋው የደረሰው ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በባህር ላይ ሲጓዝ በነበረ ጀልባ ላይ የመስጠም ችግር በማጋጠሙ እንደሆነ ነው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ያሉት፡፡
በሜድትራኒያን ባህር ላይ ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ተከስቷል በተባለው የጀልባ መስጠም ለሞት የተዳረጉት 16 ኢትዮጵያውያን ከትግራይ ክልል ወደ ሊቢያ የተጓዙ መሆናቸውን፤ የትግራይ ክልል ህዝብና መንግስት ግንኙነት ቢሮ በዛሬው ዕለት አረጋግጧል፡፡
በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት ዜጎች፤ በትግራይ ክልል “ኢሮብ” ተብላ የምትጠራው ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ከሟቾቹ መሐል አስሩ ሴቶች እንደሆኑም ተሰምቷል፡፡ የትግራይ ክልል መንግስት ባወጣው የሃዘን መግለጫ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
ሕወሓትንና ደጋፊዎቹን ያበሳጨው የመዓዛ አሸናፊ “ምሳሌ” ትክክል ነው ተባለ
በቅርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ያነሱት እና ውዝግብ የፈጠረው ሐሳብ ትክክለኛ ነው ሲሉ የፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ገለጹ፡፡
በውይይት መድረኩ፤ በሽግግሩ ወቅት ፍርድ ቤቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል የተለያዩ ሀሳቦች ተንፀባርቀው ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቷም በሃገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ክልሎች መካከል መስማማት አለመኖሩንና ችግሮች መኖራቸውን፣ የፍትህ አካላትም መውሰድ የሚገባቸውን ዕርምጃ መውሰድ በሚችሉት መጠን እየወሰዱ አለመሆኑን መጥቀሳቸው ተገቢ መሆኑን ጭምር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ ሰለሞን እጅጉ ይናገራሉ፡፡
ምሳሌው የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተፈፃሚ መሆን አለባቸው፣ እንዲፈጸሙ የሁሉም አካለት ተሳትፎ እንደሚያፈልግ ለመናገር የመዘዙት የአሜሪካው ተሞክሮና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ ንግግር ትግራይ ክልል ላይ ያነጣጠረ ነው የሚለው እሳቤ፣ የተሳሳተና አስተያየቱ ሌሎችንም ያካተተ እንደሆነ ማወቅ ይገባልም ብለዋል፡፡
“የፍርድ ቤት ትዕዛዝና ውሳኔን ለማስፈፀም ሊደረጉ ከሚገባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ማሳያ ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ዴሞክራሲያዊ የሆነ የፍትህ ሥርዓት ሰፍኖባቸው የሚታዩ ሃገራት በእንደዚህ ዓይነት ተግዳሮት ውስጥ አልፈው ነው እዚህ የደረሱት ለማለት እንደማሳያነት መጥቀሱ አግባብነት የለውም የሚል ሀሳብም፣ አቋምም የለኝም” በማለት አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የገለጹት የፌደራል ፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ የትኛውም የፍርድ ውሳኔ የማይፈፀም ከሆነ ፍርድ ቤት የለም ማለት ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ወሮ መዓዛ አሸናፊ ሰሞኑን ከህግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ፤ በአሜሪካ በ1950ዎቹ የነጮችና የጥቁሮች የትምህርት እድልን አስመልክቶ ከጥቁሮች የቀረበውንና ፍርድ ቤት የወሰነውን ግዛቷ አልበቀበልም በማለቷ፣ በወቅቱ ሃገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ድዋይት አይዞን አወር ውሳኔውን ለማስፈፀም ኃይልን ተጠቅመዋል፣ በማለት የጠቀሱት ምሳሌ በከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰትና በሌብነት የሚፈለጉት ጌታቸው አሰፋ፣ የሕወሓት ቱባ ባለስልጣናትና የጦር ጄነራሎችን ከህግ ሸሽገው ያስቀመጡ አካላትና ደጋፊዎቻቸውን ማበሳጨቱ አይዘነጋም፡፡
የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለ50 ቀናት ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ተገለጸ
ከነገ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ/ም ድረስ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግይ ሆናሉ ተብሏል፡፡
አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጡ፣ ከዜጎች መሰረታዊ መብቶች፣ ከሃገር ሰላምና ፀጥታ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደ ጊዜ ቀጠሮ ዓይነት ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች የሚስተናገዱበት አሰራር መኖሩን ተጠቁሟል፡፡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ጽሕፈት ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የዋስትና የዕግድ ጥያቄዎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች፣ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣ ከቤተሰብ፣ ከሕፃናት ቀለብና አስተዳደግ ጋር የተያያዙ አጣዳፊና መሠረታዊ ጉዳዮችም በተፋጣነ ስነ- ስርዓት በዚሁ መንገድ ይስተናገዳሉ፡፡
ፍርድ ቤቶች ለ50 ቀናት ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ፤ በዳኞችመልካም ፍቃድ የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው ወደ ቀጣዩ ዓመት የተሻገሩ መዛግብትን የማጥራት ስራ ይሰራሉ፡፡
በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ2011 እና ከዚያም በፊት የተከፈቱ መዛግብት ለምርመራ፣ እንዲሁም ብይን እናውሳኔ ለመስጠት ለ2012 የተሻገሩ 4 ሺህ 702 መዛግብትን የማጥራት ዕቅድም ተይዟል፡፡
በከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአስር በላይ የሚሆኑ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሹመው በመዘዋወራቸው ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በከፊል ዝግ የሚሆንበት ቀን በ15 ቀን ተራዝሟል፡፡
ሐምሌ በዓለም ላይ ሞቃታማው ወር ሆኖ ተመዘገበ
እስካሁን በዓለም ከተመዘገቡ ሞቃታማ ወራቶች ሁሉ የዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር ከፍተኛው ሞቃታማ ወር መሆኑን ከሳተላይት መረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በአውሮፓ ሕብረት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰራው ድርጅት ኮፐርኒክስ ፕሮግራም (c35) ነው ጥናቱን ያካሄደው፡፡ ይህ አዲስ ሪከርድ መሬት ያልተጠበቀና እንግዳ የሆነ ሙቀት እያሰተናገደች ስለመሆኗ በቂ ማሳያ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር 2016 ከተመዘገበው የሙቀት መጠን የዘንድሮው ሐምሌ 2019 በ0.04 ዲግሪ ሴልሺየስ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የ2016ቱ የሙቀት መጠን ከዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ባሻገር የኤልኒኖ የአየር ንብረት ክስተትን ተከትሎ የመጣ እንደነበር ይታወሳል፡፡
እንደ ጥናቱ ባለቤት ኮፕርኒከስ ከሆነ፣ በዚህ ዓመት በየወሩከተመዘገቡት አራት እጅግ ሞቃታማ ወሮች መካከል ሐምሌ ወር አንዱ ሲሆን፤ ይህ ክስተት በረዥም ጊዜ ሂደት ከሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት እንደሌለውም ይፋ አድርገዋል፡፡