የጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ ዛቻ ፣የቴሌ ሹሟ ተማጽኖ || ታምሩ ገዳ

የጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ ዛቻ ፣የቴሌ ሹሟ ተማጽኖ || ታምሩ ገዳ

ለተወሰኑ ጊዜያት ከጋዜጠኞች የፊት ለፊት ግንኙነት (ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት )ርቀው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር እብይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዬች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።

ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ከአለማቀፍ የመረጃ አገልግሎቶች አንዱ አካል የሆነው የኢንተርኔት ስርጭትን በተለያዩ አጋጣሚዎች እና አስባቦች ለተወሰኑ ቀናት የመዘጋቱ ጉዳይን በተመለከተ ነበር።

የጠ/ሚ/ር አብይ ምላሻቸውም ” ኢንተርኔት ውሃ አይደለም፣ኢንተርኔት ማለት አየር ማለት አይደለም”ያሉት ዶ/ር አብይ ባለፈው ሰኔ ወር በባሕር ዳር እና በአ/አ ከተሞች ላይ በክልል እና በፊደራል ባለስልጣናት ላይ የተቃጣው የግድያ እርምጃን ተከትሎ በአገሪቱ ሙሉ በሙሉ የኤንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ “ተጨማሪ የሰው ህይወት ከማጥፋት ረገድ” ተገቢ እና ፍትሀዊ እንደሆነ ፣ “ኢንተርኔት ለህይወት ጥፋት ፣ለንብረት ውድመት መቀስቀሻ የሚውል ከሆነ ለቀናት አይደለም ለረጅም ጊዜ ይቋረጣል ። በኢንተርኔት ሳቢያ የአንድ ሰው ህይወት ከሚጠፋ፣አንተርኔት ቢከረቸም፣ ከኢንተር የሚገኘው የኢኮነሚ ኪሳራንም ብንጋፈጥ እንመርጣልን ” ሲሉም ተደምጠዋል ።

ዶ/ር አብይ አሕመድ በኢንተርኔት አቅርቦት ዙሪያ ስላለው የመንግስታቸው አቋምን የገለጹበት መንገድ ኢትዬጵያኖችን ሆነ ለመረጃ ቅርብ የሆኑ የአለማቀፉ ማህበራትን ከሁለት የተለያዩ የአመለካከት ጎራዎች መክፈሉ አልቀረም።

ለምሳሌ ያህል ጎረቤትህ ሲታማ ስለ እኔ ብለህ ስማ እንዲሉ የጠቅላዩን አስተያየት በኬኒያው (ዘ ስታር ጋዜጣ) አማካኝነት ያነበቡ ኬኒያዊያን አስተያየት ሰጪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኪንግ ሚኒስ የተባሉ” የኢንተርኔት ዳታ አጠቃቀሙ ከ11% ላልበለጠ ለኢትዬጵያ ህዝብ ኢንተርኔት የሚባል ነገር ከውሃ ጋር በጭራሽ አይወዳደርም ፣ዶ/ር አብይ በዚህ አባባላቸው ትክክል ናቸው ፣ነገር ግን የኢትዬጵያኖች የኢንተርኔት የዳታ አጠቃቀሙ እንደ ኬንያዊያኖች 90%ሲደርስ ዶ/ር አብይ ተመሳሳይ አስተያየት ይሰጡ፣ አይሰጡ እንደሆነ የዚያን ጊዜ እንመለከታቸዋለን “በማለት የዶር አብን አቋምን ለጊዜው ደግፈዋል።
የኢንተርኔት አገልግሎት ከህይወታቸው ጋር መቆራኘቱን የሚናገሩት ማይክ የተባሉ በበኩላቸው” እኔ በግሌ ስራዬ ከኢንተርኔት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ያለ ኢንተርኔት መኖር አልችልም “በማለት በኢንተርኔት ላይ የሚደረጉ ቀጥተኛ ይሁኑ ስውር ማእቀቦችን እንደማይደግፉ ይገልጻሉ።

ኖኦ ማቱሱ የተባሉ እንዲሁ ” በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ከውሃ እኩል ጠቀሚታ አለው።ሊላልው ቢቀር ገንዘብ እንኳን ከባንክ ለማውጣት ከሂሳብ ሰራተኛ ጋር መፍጠር ቀርቷል፣ የኢንተርኔት አገልግሎት የግድ ያስፈልጋል ” ። በማለት ኢንተርኔት እንደ አየር እንደ ውሃ እንደ ጨው እና እንደ ዳቦ ከህይወታችን ጋር መቆራኘቱን ለመግለጽ ይሞክራሉ። አንዳንድ ኢትዬጵያኖችም በበኩላቸው ሌላው ቢቀር “ኢትዬጵያ በአረንጓዴው ግብይት አለምን ያስደነቀችበት ሰሞነኛ ዜና ከጠ/ሚ/ሩ ቢሮ ፣ከራሳቸው የትዊተር ገጽ በተለጠፈው ውብ ፎቶዎች አማካኝነት አይደለም እንዴ?” ሲሉ ስለ ኢንተርኔት አስፈላጊነት ይከራከራሉ።

ምንም እንኳን ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ “ኢንተርኔት ለጥፋት የሚውል ከሆነ ዳግም ሊዘጋ ይችላል” አይነት ማስፈራሪያ ቢሰጡም በኢትዬጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ ፣ዘገምተኛ ሲሆን፣ አንዳንድ ድህረገጾች ሲታገዱ፣ጋዜጠኞች፣ፓለቲከኞች ፣አክቲቪስቶች…. ወዘተ ኢሜሎቻቸውእና ስልኮቻቸው ሲበረበሩ በቀጥታም ይሁን በገደምዳሜ ዋንኛ ተባባሪ የሆነው መንግስታዊው የኢትዬ ቴሌኮም(ቴሌ) ዋና ሹም የሆኑት ወ/ት ሰላማዊት ታምሩ በቅርቡ የ2011 ዓም አመታዊ የድርጅታቸው ሪፖርትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ” መንግስት ከፍተኛው የአገሪቱ ገቢውን የሚያገኘው ከኢትዬ ቴሌኮም በመሆኑ ቴሌ ታወከ ማለት ለልማት የሚወጣው የገንዘብ ምንጭ ይታወካል፣ ኢንተርኔትን የመዝጋት ፍላጎት የለንም ፣አገራችንም እኛም ገና በመሰራት ላይ ነን (የተጠናቀቀ ሲስተም የሚባል ነገር የለንም) ፣በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበሩ ችግሮች ሳቢያ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት ባለመቻላችን በጣም ይቅርታ አድርጉልን ፣ወደፊት ደምበኞች ሳይታወኩ አገልግሎታችንን የምንሰጥበት መንገድን እንቀይሳለን ” በማለት መማጸናቸው አይዘነጋም።

ይሁን እና በአገሪቱ ውስጥ ኮሽ ባለ ቁጥር ወይም ባለስልጣናት ሲጣሉ ሆነ ሲደብራቸው እንደ ቦኖ ውሃ የሚዘጋው እና የሚከፈተው የኢትዬጵያ ኢንተርኔትን የሚዘውረው ኢትዬ-ቴሌኮም ደንበኞቹንም ሆነ ጌቶቹን ሳያድቀይም ወደፊት ውጤታማ አገልግሎት እንዴት እንደሚሰጥ ከፈጣሪ እና ከእነርሱ በቀር ለጊዜው ማንም አያውቅም ።

በኢሕአዲግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ሳይቀር “የማትነጥፈዋ ላም ” የሚል የቁልምጫ መጠሪያ ስያሜ የተሰጠው ኢትዬ -ቴሌ በአለማቀፍ የኢንተርኔት ፈሰስ አጥኚው (ኔት ብልክ)ግምት ኢትዬጵያ በተማሪዎች ፈተና ምክንያት ይሁን በጸጥታ መደፍረስ የተነሳ ኢንተርኔት በተቋረጠባቸው ሰሞናት በቀን 4.5 ሚሊዬን ዶላር ማጣቷን ገልጿል ።ይሁንና “የማትነጥፈዋ ላም ” ሹሟ ወ/ት ፍሬህይወት በበኩላቸው ” ባለፈው አመት ከድምጽ ወደ ዳታ(ወደ ኢንተርኔት ) አጠቃቀማችን ከ11% ወደ 29% አድጎል፣አመታዊ ትርፋችንም 36.3 ቢሊዬን ብር ሲሆን ኪሳራችን ግን 204 ሚሊዬን ብር ብቻ ነው”በማለት ማስተባበላቸው አይዘነጋም ። እለታዊ እንቅስቃሴያቸው ከኢንተርኔት ጋር የተዛመደ አገር በቀል እና አለማቀፍ ድርጅቶች በመንግስት ጫና ስለደረሰባቸው የገንዘብ እና የደምበኞች ኪሳራ የቴሌ ሹሟ ለጊዜው ያሉት ነገር የለም ።ነገሩ ያው እንደተለመደው” መንግስት አይከሰስ ንጉስም አይወቀስ “አይነት መሆኑ ነው።

መንግስታት ኢንተርኔትን ለምን ያፍናሉ?:-

ምንም እንኳን ለኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የሚሰጠው ምክንያት በአብዛኛው ” የህዝብን ደህንነት እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ነው (Public security & Order)ተብሎ ቢነገርለትም እንደ ኮንቨርሴሽን ድህረ ገጽ ትንታኔ ኢንተርኔት የብዙዎች መገናኛ ድልድይ በሆነበት በዚህ ዘመን በርካታ መንግስታት (ኢትዬጵያን ጨምሮ) ኢንተርኔትን እንደ ጦር ስለሚፈሩ የፖለቲካ ትኩሳቱ ሲጋጋም ለህዝቡ ደህንነት በመስጋት ሳይሆን ለፖለቲካ መደላድላቸው ሲሉ ኢንተርኔትን በመዝጋት ጭንቀታቸውን ለማብረጃ መንገድነት ይጠቀሙበታል።

በአሁኑ ወቅት 6 ቢሊዬን የዓለም ሕዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆን በአብዛኛው አገራት የአገልግሎቱ እና የተደራሽነቱ ፍጥነት ከቀድሞው ከፖሊስ ቁጥጥር የፈጠነ እና የረቀቀ በመሆኑ እንደ ኢትዬጵያ የፖለቲካ እንከን ያለባቸው አገራት የህዝቡን አፍ ለማዘጋት ኢንተርኔት ላይ ያተኩራሉ። ሌላው ጉዳይ ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን( ስራዬ ብለው ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚመግቡ መኖራቸው ሳንዘነጋ ) በማህበራዊ ድህረ ገጾች እንደ ፌስ ቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስ አፕ ኢንስትግራም፣ ቴሌግራም በመሳሰሉት አማካኝነት በፈጣን መንገድ ወደ ሕዝቡ ሲያደርሱ አምባገነን ገዢዎች ሰላም እና እንቅልፍ ይነሳቸዎል። ሰለዚህ እንደ ኢትዬ- ቴሌኮም አይነት ተቋማት በኢንተርኔት ላይ ሙሉ በሙሉ ፣በከፊል አሊያም ዘገምተኛ (ፍጥነቱን በማዳከም) ክልከላ እንዲያደርጉ ይታዘዛሉ። እርምጃዎቹን መንግስታት የደህንነት ዋስትና ለማስፈን ነው ቢሉትም የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው “ሳንሱር በጓሮ መጣች” ባይ ናቸው።

የአለማችን አፍቃሪ እና ጸረ- ኢንተርኔት አገራት:-

የዘመናችን የሰው ልጆች መሰረታዊ መገልገያ የሆነው ኢንተርኔትን በማወክ ረገድ ቀደም ያለ የፍሪደም ሀውስ ጥናታዊ መረጃ እንደሚገልጸው ከሆነ ኢትዬጵያ፣ ኤርትራ፣ ዙምባብዌ፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ ሰውዲ አረቢያ፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ቬተናም፣ ናይማር (በርማ)፣ ሰሜን ኮሪያ የጎደፈ ስም አላቸው። ኢንተርኔትን ለሕዝባቸው በተገቢው መልክ በማቅረብ መልካም ስም ካገኙት አገራት መካከል ትንሿ አገር አይስላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ እና አሜሪካ ይከታተላሉ።

ኢንተርኔትን አገልግሎትን ማወክ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል?

እንደ አለማቀፉ የነጻነት ተቋም (ፍሪደም ሀውስ) ምልከታ የኢንተርኔት አገልግሎት ልክ እንደ ፏፏቴ ውሃ ፍሰት ሊቋረጥ የማይገባው ለኑራችን ፣ለአይምሮ ሆነ ለአይን የሚማርክ የዘመናችን የጥበብ ውጤት ነው።

ከዚህ አኳያ ኢንተርኔት በተዘጋ ቁጥር ዜጎች ለምን ተዘጋ ብለው ይጠይቃሉ ፣እንቨስተሮች ይደናገጣሉ ።የኢንተርኔት መዘጋት የሰዎችን ተፈጥሮአዊ የመሰብሰብ መብትን አያግደውም።አሉባታ ወሬዎችን የማነፍነፍ ጉጉታችንን ይጨምራል እንጂ አያስቆመውም ። አዳም እና ሔዋን ያ ሁሉ ምግብ ተፈቅዶላቸው የተከለከለው እፅ በለሰ እንደጎመዡ፣ኋላም እንደወደቁ ሁሉ የኢንተርኔት ማነቆ እና ክልከላም እንዲሁ ጊዜያዊ ፋታ ካልሆነ በቀር ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም፣ሰዎችንም ቢሆን እንዲሸፍቱ እና ተጠርጣሪዎች እንዲሆኑ ከመገፋፋት ውጪ ወደ ልቦናቸው በቀላሉ እንዲመለሱ አያደርግም የሚሉ ወገኖች በርካታዎች ናቸው።

LEAVE A REPLY