በ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና አማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት አስመዘገበ

በ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና አማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት አስመዘገበ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዘንድሮው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሃገር አቀፍ ፈተና የተመዘገበው ከፍተኛው ውጤት 645 ሲሆን፤ ይህ ውጤትም በአማራ ክልል መመዝገቡን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃረጓ ማሞ ገለፁ::

ውጤቱን ያስመዘገበውም ብሩክ ዘውዱ የተባለ በባህርዳር የአየለች ደገፉ መታሰቢያ (ሐይሌ) ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ተሰፈኛውን ወጣት እና ወላጅ እናቱን በስልክ አነጋግሯቸዋል::

ውጤቱን እንደሚያመጣ ይጠብቅ የነበረው ተማሪ ብሩክ ብዙም እንዳልተደነቀ ገልፆ በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ይህን ያህል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ቀዳሚ እሆናለሁ የሚል ግምት እንዳልነበረው አልሸሸገም:

“ሁሉም ሰው የራሱ ሆነ የጥናት ስልት አለው፤ የእኔ የንባብ ስልት ለሌላው ላይፈይድ ይችላል ” የሚለው ብሩክ በፕሮግራም፣ ብዙም ሳይጨናነቅ ዘና ብሎ እንደሚያጠና በመግለፅ ልምዱን ለሌሎች አካፍሏል::

የአስር ዓመት ልጅ እያለ አባቱን በሞት የተነጠቀው የባህር ዳሩ ከዚያ ብሩክ  በኋላ የእናትንም የአባትንም ቦታ ተክተው ያሰደጉት እናቱ ናቸው::

ብሩክ በጤና ዘርፍ፣ በኮምፒዩተር ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የመማር ፍላጎት ቢኖረውም እስካሁን ግን ቁርጥ ያለው ውሳኔ ላይ አልደረሰም። ይሁን እንጂ ወደ ሕክምናው ዘርፍ ሳያደላ እንደማይቀር ተናግሯል::

“ደስታ ያሰክራል፤ ደስታ እንባ እንባ ይላል”  በማለት በልጃቸው ውጤት እንደተደሰቱ የተናገሩት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ጥላሁን ናቸው።

“ራሱ ስልክ ደውሎ፤ እንዳትደነግጭ፤ ስድስት መቶ ምናምን አምጥቻለሁ ብሎ ስልኩን ዘጋው” በማለት የምስራቹን የሰሙበትን መንገድ ያስታውሳሉ:: ጥቂት ቆይቶ ጓደኛው ደውሎ ብሩክ ከኢትዮጵያ ተፈታኞች አንደኛ እንደወጣ ሲነግራቸው ደስታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉም ይፋ አድርገዋል::

” በሰዓቱ አብራኝ የነበረች ጓደኛዬን አቅፌ ጮህኩ፤ እሷን አቅፌ አለቀስኩ፣ ተንበረከኩ.ፈጣሪን አመሰገንኩ”  የሚሉት

“እናንተ የምታስመዘግቡት ውጤት ለእኔ ደመወዜ ነው እያልኩ ስለማሳድጋቸው ተግተው ነው የሚሰሩት ” ይላሉ። መልካም ውጤት ሲያመጡም ደመወዝ እንደከፈሉኝ ነው የሚሰማቸው ሲሉ ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ተግባቦት በአርአያነት ጠቅሰዋል::

“የምንኖረው ሁለት ክፍል ቤቶችን እያከራየን ነው፤ ለልጆቼ የማወርሳቸው ምንም ሀብት የለኝም” የሚሉት ወ/ሮ ኤልሳ እነርሱ ላይ ፍሬያቸውን ማየት እፈልጋለሁ ብሩክ በተሰማራበት ሁሉ ውጤታማ መሆን የሚችል ልጅ ነው፤ የሞከረው ሁሉ ይሳካል” የሚሉት ወ/ሮ ኤልሳ ብዙ ጊዜ ናሳ የመሄድ ምኞት እንዳለው ተናግረዋል::

የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 322 ሺህ 717 ተማሪዎች መካከል 319,264 የሚሆኑት ፈተናውን መውሰዳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ ገፁ አስታውቋል። ፈተና ላይ ከተቀመጡት ውስጥም 59 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ሲያመጡ 48.59 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ350 በላይ ውጤት አምጥተዋል። በፈተናው ወቅት በተፈጸመ የደንብ ጥሰት የ68 ተማሪዎች ውጤት እንደተሰረዘም ኤጀንሲው አረጋግጧል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ፈተናው በመሰረቁ ነው የሚሉ የፈጠራ ወሬዎች እና ውጤቱን ከዘር ፖለቲካ ጋር በማቆራኘት ተራ ፕሮፐጋንዳዎች በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት ተጀምሯል:: ውጤቱ ከተገለጸበት ዛሬ ማለዳ ጀምሮ የተያዘው የአማራ ክልልና ሕዝብን የማጣጣል ዘመቻ በርካቶችን እያስቆጣ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ  በሰፊው የተዘረጋው ዘርና ጎሣ ተኮር የፖለቲካ ጉዞ ወጣቶችን በዩኒቨርሲቲ እና በኳስ ሜዳ ብቻ ሳይሆን በወሰዱት የፈተና ውጤት ላይ ሳይቀር  የሚያደርገው ዘግናኝ መጠላለፍ ወደ ህጻናት መዋያ ዘልቆ የሃገሪቱን ህልውና እንዳይተላለፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በትንሽ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች የሚቀነቀነው የብሔር ፖለቲካ የእልቂት ጥግ ላይ እያደረሰን ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገለጸዋል።

ሃገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ የዘንድሮው የማትሪክ ፈተና ያለምንም ችግር በሰላም መጠናቀቁን ከሳምንታት በፊት መግለፁ አይዘነጋም::

LEAVE A REPLY