አርአያ ገ/እግዚአብሔር – አዲስ ከተማ – መድሓኔዓለም – ፈተና – የዘር ፖለቲካ...

አርአያ ገ/እግዚአብሔር – አዲስ ከተማ – መድሓኔዓለም – ፈተና – የዘር ፖለቲካ || አቤል ዋበላ

አርአያ ገ/እግዚአብሔር አዲስ ከተማ ሁለተኛ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ስማር የት/ቤቱ ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ ለማቅረብ ነበር እያልኩኝ እቀጥላለኹ፡፡ እዚያ በነበረኝ ትዝታ ለአርአያ ያለን አመለካከት በጣም በጎ የሚባል ነበር፡፡ ብዙኃኑ ተማሪ የአርአያ ወዳጅ ነበር፡፡ ት/ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲያዘግም ጥጋችንን ይዘን ስንመለከተው ትዝ ይለኛል፡፡ በተለይ ቤተ መጽሐፍት አከባቢ ለማንጠፋ ልጆች ይህ የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነበር፡፡ እርሱም ከተማሪው ጋር የነበረው ቅርርብ ደስ የሚል ነበር፡፡

ትዝ ይለኛል የቤተ መጽሐፍቱ አለቃ ጋሽ ታሜ የሚባሉ ሰውዬ ናቸው፡፡ ያን ሁሉ ውሪ ቲኔጀር በስርዓት አሰልፈው አስገብተው እንዲጠቀም የሚያደርጉት እሳቸው ነበሩ፡፡ የጠንካራ ዲሲፕሊን ሰው ናቸው፡፡ ውልፍት ያለውን ከመቅጣት አይመለሱም፡፡ የተማሪው ብዛት እና የቤተ መጽሐፍቱ ወንበሮች አይመጣጠኑም፡፡ በተማሪው በብዛት የሚፈለጉ አንዳንድ መጽሐፍት ደግሞ እጥረት ነበር፡፡ ወሬ ሁካታ ደግሞ አፍላ ወጣት በበዛበት እንደጉድ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ስርዓት የሚያሲዝ ሰው ያስፈልግ ነበር፡፡ ጋሽ ታሜ ለዚህ ሁነኛ ሰው ነበሩ፡፡ ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ የአስራኛ እና አስራ ሁለተኛ ተማሪዎች ቅድሚያ ይገባሉ በቀረው ቦታ ሌሎቻችን እንሰገሰጋለን፡፡ ጋሽ ታሜ ሲሞላ በቃ ብለው ይመልሳሉ፡፡ አርአያ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲያዘግም እና ከምሳ ሲመለስ እግረ መንገዱን ወደቤተ መጻሕፍት ጎራ ይላል፡፡ ላይብረሪው ሞልቶብን በር አከባቢ የቆምነውን ልጆች ይዞ ወደ ውስጥ ይገባል፡፡ ክፍት ቦታ በተገኘበት እና ቤተ መጽሐፍቱ መሀል አከባቢ የሚገኝ ደረጃ ላይ እንድንቀመጥ ያደርጋል፡፡ ይህ በልጅ አእምሮዬ እንደትልቅ ውለታ የቆጠርኩለት ነው፡፡

ሌሎችም ስለ አርአያ መልካምነት የሚያወሱ በጎ በጎ ተረኮች ነበሩ፡፡ ከሰማኹትን ውስጥ አንዱን ላጫውታችኹ፡፡ ዩኒት ሊደሮች የሀይስኩል ፈላጭ ቆራጭ ናቸው፡፡ አርፍዶ የመጣን ወይንም ከመምህራን ጋር በክፍል ውስጥ አተካራ የሚፈጥር ተማሪ ለዩኒት ሊደር ቅጣት እና ቁጣ ሲሳይ ይሆናል፡፡ ታዲያ ተማሪዎች በስንፍናም ይሁን በሌላ ምክንያት አርፍደው ሲመጡ የት/ቤቱ በር አከባቢ ወደነበረው የአርአያ ቢሮ ጋር ይደርሳሉ፡፡ አርአያ እንደ ዩኒት ሊደር ማንበርከክ ወይም መታወቂያ መቀማት ውስጥ አይሳተፍም፡፡ ግራ እና ቀኝ አይቶ ዩኒት ሊደሩ በሌለበት በኩል በዚህ ሂዱ ብሎ ተማሪዎችን ይሸኛል፡፡ ይህም ለተማሪ ታላቅ ውለታ ነው፡፡

አስረኛ ክፍል ተፈትነን መሰናዶ ስንመደብ እኔ መድኃኔዓለም ተመደብኩኝ፡፡ ከለመድኩት ግቢ እና ከጓደኞቼ መነጠልን ስላልፈለኩኝ ቀጥታ ወደ አርአያ ቢሮ ገባኹኝ፡፡ ጉዳዬን ባጭሩ አስረዳኹኝ፡፡ እንደሚረዳኝ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ እስኪ አንድ ሴሜስተር እዚያ ተማር እና የሚሆነውን እናያለን አለኝ፡፡ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ መድኃኔዓለም በባስም በታክሲም እየተመላለስኩኝ ተማርኩኝ፡፡ መንፈቀ ዓመቱ ሲያልቅ ወደ የምደወደው አዲስ ከቴ እመለሳለኹ ብዬ ሳስብ አርአያ ራሱ ወደ መድኃኔዓለም መጣ፡፡ አንድ ሴሜስተር ታገስ ያለኝ ሊያታልለኝ ፈልጎ ይሁን ወይስ ራሱም ወደ መድሽ እንደሚመጣ ስላወቀ? አላውቅም፡፡

መድሽ ከተቀየረም በኋላ በሚታይ መልኩ ትምህርት ቤቱ እንዲሻሻል ተማሪው ይበልጥ ተመችቶት ቀለም ላይ እንዲያተኩር የሚያርጉ ስራዎችን ይስራ ነበር፡፡

ከአመታት በኋላ የቀድሞ ርዕሰ መምህሬ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጄንሲ ኃላፊ ሆነው እንደሚሰሩ ከሚዲያ ሰማኹኝ፡፡ ተገቢ ኃላፊነት እንደሆነ አመንኩኝ፡፡ ምክንያቱም በርዕሰ መምህሬ ታታሪነት እና መልካምነት አምናለኹና፡፡
ከጊዜ በኋላ ይህንን እንደዐለት የጠነከረ እምነቴን የሚፈታተን ወሬ አንድ ወዳጄ አጫወተኝ፡፡ ተረኩ አርአያ ገ/እግዚአብሔር ከፈተናዎች አጀንሲው ሠራተኞች ጋር መስማማት አልቻሉም አምባገነነን ናቸው የሚል ነው፡፡ በዚህ የተበሳጩት ሠራተኞች በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ለነበረው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አቤት ይላሉ፡፡ ሽፈራውም የብዙኃኑ ሠራተኛን ጫጫታ ለመቀነስ አርኣያ ግብረ እግዚአብሔርን ከቦታው አንስቶ ሌላ ሰው ይሾማል፡፡ እንደ ወዳጄ ትረካ ይህ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ አሁን መቀሌ ሄደው የሚተውኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ሽፈራውን ተቆጥተው አርአያን ወደወንበሩ መለሱት፡፡ ይህ ወሬ ልቤን አሳመመው፡፡ እንዴት አርአያ ሥራውን ለማከናወን የወያኔ ድጋፍ ያስፈልገዋል? በቅርብ የተመለከትኩት ታታሪነት እና መልካም ስብዕና ወዴት ሄደ? ብዬ በልጅነቴ ከያዝኩት እውነት ጋር ሙግት ገጠምኩኝ፡፡

አርአያ ጃዋር መሐመድ ፈተና እየሰረቀ በሚበትንበት ጊዜ ብዙ ተፈትኗል፡፡ የሰራቂዎቹ ተባባሪ እንዳይደለ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ፈተናው ደግሞ የሚሰረቀው አጀንሲው አከባቢ በተዘረጋው በኦህዴድ መረብ አማካኝነት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሽማግሌዎቹ ወያኔዎች አርአያን ምን ሊሉት እንደሚችሉ ማሰብ አእምሮን የሚፈትን ነው፡፡ በየትኛው የቁጥጥር ስርኣት ከላይ ሲታዩ ኦህዴድ ውስጣቸው ግን ኦነግ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መከታተል ይችላል?

እርግጥ ነው ቀድሞ የነበረው የፈተና ስርቆት የሞራል ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ሀቲት ነበረው፡፡ ከፊሉ ፖለቲካዊ ተጽእኖ ለመፍጠር ሲባል በታዳጊዎች ህይወት ላይ መጥፎ አሻራውን የሚያሳርፍ ነገር መደረግ እንደሌለበት ሲናገሩ ከፊሉ ደግሞ ለውጡ ሀገራዊ ነው እነርሱም በፖለቲካ ለውጡ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ዴሞክራሲ ቢመጣ የነገ ተስፋቸው ይለመልማል፡፡ በዚያ ላይ መንግስት ንጹኃንን እየገደለ እና እያሰረ በስልጣን መቆየቱ ልክ አይደለም የልጆቹ መጎሳቆል ጊዚያዊ ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡

እኔ ወደ ሁለተኛው እያደላኹኝ ግን የተገቡት ተስፋዎችን እርግጠኝነት እጠይቃለኹ፡፡ እውን ፈተና ሲሲርቁ እና ሲያሰርቁ የነበሩ ሰዎች የኢትዮጰያ ወጣቶች በሙሉ በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እንድትኖራቸው ይፈልጋሉ ወይ? ብዬ እጠይቃኹ፡፡ ያለፉት አስራ ምናምን ወራት ያለጥርጥር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውናል፡፡ ፈተና ዘራፊዎቹ ዘረኞች ብሎም የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጠላቶች መሆናቸው በተግባር ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ እንድትኖርም እንድትጠፋም የሚፈልጉት ለእነርሱ ሰፈር ሰው፣ የእነርሱን ቋንቋ ለሚናገር፣ በአጎት ልጅነት እና በአክትስት ልጅ ለሚዛመዳቸው ሰው ምቾት ነው፡፡ ስለዚህ ተፈትነው ስለወደቁ ቀድሞ የተሳተፉበት ተግባር ከሞራላዊነት ይልቅ ወደ ወንጀል ያዳላል፡፡

የሰሞኑን ግርግር ደግሞ የሰማኹት ደግሞ የቲቪዬን ሪሞት ወዲያ ወዲህ ሳመላልስ የቀድሞ ርዕሰ መምህሬ ስለሀገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤት መግለጫ ሲሰጡ በማግኘቴ ነው፡፡ የተማሪዎቹን ውጤት ጥቅል ስታስቲክ ሲያስረዱ “…ከፍተኛ ውጤት የመጣው 645 ነጥብ ነው፡፡ ከአማራ ክልል ነው የተገኘው፡፡…” ማለታቸውን ቀድሞም ነገሮችን በጥርጣሬ የሚመለከተው ቀልቤ ለምን ልጁ የሚኖርበትን ከተማ ወይም ትምህርት ቤት አልጠቀሱም እያለ ሲያመነዥክ አደረ፡፡ በንጋታው የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተናውን ውጤት አልቀበለም አለ የሚለው ዜና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ይኖረው ይሆን?

አሁን ባንድ ወገን አማራ ክልል ፈተናዎቹ ቀድሞ ለተማሪዎች ታድሏል የሚል ክስ ሲቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ በጎጣቸው ልጆች ምጡቅ አእምሮ የሚደመሙ ሆነዋል፡፡ ጎጥ ቤተ መጽሕፍት ገብቶ ቁጭ ብሎ አያጠናም፡፡ ጥሩ ውጤት ያመጣም ቢኖር ሊደሰቱ እና ክሬዲቱን ሊወስዱ የሚገባቸው ለፍተው ልጆቻቸውን ያስተማሩ ወላጆች እና መምህራን ናቸው፡፡ ሌላው ደስታ የሰው ልጅ በጎ ነገርን ሲያደርግ ከሚሰማ ሰዋዊ ደስታ የዘለለ መሆን የለበትም፡፡

የቀድሞው ሞራላዊ ክርክር ዳግም ተነስቷል፡፡ ፈተና ሰርቆ የራሴ ለሚሉት ለብሔረሰብ ማደል ተገቢ ነው አይደለም የሚል ሙግት አለ፡፡ አሁንም ሞራላዊ ክርክር ሲነሳ ድርጊቱ ሲፈጸም በማኀበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው የአጭር እና ረጅም ጊዜ ተጽእኖን መለካት የአእምሮ ብይን ለመስጠት ይረዳል፡፡ ለእኔ እያንዳንዱ ጉዳይ ከኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠል ህልውና እና ቅርጽ ጋር ይያየዛል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያ መቀጠል አለባት የሚለው ክርክር ውሃ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ፍትህ እና እኩልነት የሌለባት ኢትዮጵያ ዝም ብለን ሀገራችንን ስለምንወድ ብቻ ትቀጥል ብንል በዚህ ክፍለ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች በተለይም አፍላ ወጣቶች ላይ ሞራላዊ ፍርድን አናደርግም፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደሀገር ትቀጥል ካልን በሰው ሰውኛው በሚቻለው መጠን ፍትህ እና እኩልነት በሚያስፍን ጎዳና ነው፡፡ በፈተናውም ሆነ በሌሎች ተግባሮች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ለዚህ ኢትዮጵያን ወደ ፍትሕ ጎዳና በሚመራ፣ ካልሆነም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፈርሳ ነገር ግን በአከባቢው ለሚኖሩ ህዝቦች የተሻለ ስርዓተ መንግሥት ያላቸው ሀገራት ተፈጥረው ህዝቦች በሰላም እና በመከባበር በየሀገራቸው የሚኖሩበት ሁኔታ በመፍጠር ያላቸውን ሚና መለካት ልክ ናቸው ወይም አይደሉም ለማለት ያስችላል፡፡

የኢትዮጵያ ነበራዊ ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ቅርጿ ፍትሃዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነውን በዘር ላይ የተመሰረተ ስርዓት ላይም የማይደራደር ነው፡፡ ሀገራዊ ተጽእኖ በሚያሳድሩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች ይህንን ታሳቢ አድርገው ቢንቀሳቀሱ እና የኔ ነው ለሚሉት ወገን በሚያደላ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ቢገኙ አይፈረድባቸውም፡፡ ምክንያቱም ዘረኝነት የሀገሪቱ ሕግ ነው፡፡ ይህንን ሳይረዳ በሞኝነት እኩልነት የሚሰብክ ሰው ብዙ ያልተረዳው ነገር አለ ወይም የአእምሮው ሚዛን ፍትሕን የሚረዳበት መንገድ የተንጋደደ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡

ሀገሪቱ ዘጠኝ ትሁን አንድ ሳይለይላት የራሱን ቤት ሳያዘጋጅ የሚቆም የኔ ቢጤ ሞኝ ነው፡፡ የኔ ቢጤ የሚመኘው በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ በእውቀት ኮትኩተው እንዳሳደጉን ለሁላችንም አባት የሚሆኑን እንደ አርአያ ያሉ ሰዎች ሀገር ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ኢህአዴግ አይፈቅድም፡፡ ኢህአዴግ መገንባት የሚፈልገው በዓለም ካርታ ኢትዮጵያ የምትባል ነገር ግን ውስጧ ሲከፈት ዘጠኝ ኩርማን ሀገሮች የሚገኙባት ምድርን ነው፡፡

LEAVE A REPLY